May 17, 2014

እውነታ + እውቅና + ፍትህ = እርቅ (ያዬ አበበ)

 የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ለዚህ ተተኪ ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርዓያነት ማውረስ አስፈላጊነት ስላመንኩበት ስለ እርቅና መግባባት ለመሟገትና ፋና ወጊ ሚና ለመጫወት የዜግነት ሃላፊነቴን ጀምሬያለሁ።
ሰዎች እርቅን የተለያዬ ትርጉም እንደሚሰጡት የ65Percent.org ድረ-ገጽን ከጀመርኩበት ከዚህ አመት አጥቢያ አንስቶ እየተረዳሁ ነው። ድረ-ገጼን ከመጀመሬ በፊት ከ16 ኢትዮጵያውያን ጋር በፓልቶክ የፖለቲካ መወያያ ክፍሎች የሃሳብ አሰሳ አድርጌያለሁ። ከአሰሳው እንደተረዳሁት ስለእርቅ እና ፖለቲካዊ መግባባት በቂ የሚዲያ ሽፋንም ሆነ ውይይት አልተደረገም።
ለአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ከትጥቅ ትግልና ከአመጽ የላቀ አማራጭ አለን፦ የእርቅና መግባባት አማራጭ። በዚህ አጭር ጽሁፍ  ሰለፖለቲካዊ እርቅና መግባባት በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ጥቂት አጠቃላይ ነጥቦችን እዳስሳለሁ።

ሁለት ጭብጦች፦ ውጥረትና አለመግባባት

አንደኛ፦ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስርአትና ሂደት በውጥረት ውስጥ ይገኛል። ሁለተኛ፦ የአገራችን ፖለቲካ በእጅጉ ባለመግባባት የተጠመደ ነው። እነዚህ ሁለት ጭብጦች የአደባባይ ሚስጥር ቢሆኑም መፍትሄ ለመቅረጽ በነዚህ ነጥቦች ላይ መስማማቱ እንደ ቅደመ ሁኔታ እመለከተዋለሁ። ውጥረትና አለመግባባት የሰፈነበትን ፖለቲካችንን ማርገብና ማግባባት መሰረታዊ የእርቅ ግብ ነው።

መደበኛ ፓለቲካዊ ሂደት
የፓለቲካችንን ውጥረት ማርገብ ለፓለቲካዊ መግባባት ሁኔታዎችን ያመቻቻል። የአገራችን ፖለቲካ ላለፉት 40 አመታት ከነውጥ  ወደ ቀውስ ፤ ከአመጽ ወደ እልቂት ፤ ከቁስል ወደ ቂምና ጥላቻ ሲገለባበጥ የቆየ ነው። ፖለቲካችን መደበኛ ሆኖ አያቅም። መደበኛ ፓለቲካዊ ሂደት ማለት ከቀውስ ፥ ከደም መፋሰስ ፥ ከአላስፈላጊ ውጥረትና ከጥላቻ ውጥቶ ፥ ወደ ሚዛናዊ የሃሳብ ፉክክርና ፍትሃዊ ሂደት ውስጥ የገባ ማለት ነው።

ፓለቲካዊ ቅራኔ

የፓለቲካዊ ውጥረታችን መንስኤው ፓለቲካዊ ቅራኔ ነው። የአገራችን ፓለቲካዊ ውጥረት የብዙ ዘመናት ፡ የልዩ-ልዩ ድርብርብ ቁስሎች ፡ ቁርሾዎች ፡ ያልተቋጩ ታሪካዊ ክስተቶች ፡  ርዮተአለሞች ፡ ማንነቶች ፡ ስሜቶች … ወዘተ ውጤት ነው። እነዚህ ድርብርብና ዘርፈ-ብዙ የቅራኔ መንስኤዎች አልፎ አልፎ ምልክታዊ ትኩረት አግኝተዋል። እንደ ዋቢ ከሚጠቀሱት አንዱ የቀይ ሽብር መታሰቢያ ሙዚየም ሲሆን ፡ ሌላው የወታደራዊው መንግስት ባለስልጣናት ከእስር መለቀቅ ነው።


ሆኖም ግን የፖለቲካ ቅራኔያችን ሲባባስ ፥ የፖለቲካ ምህዳር ሲጠብ ፥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመድብለ ፓርቲ ስርአት ወደ አሃዳዊ ፓርቲ ቁጥጥር ሲያዘነብል እንጂ ፡ ወደ መደበኛ ፖለቲካዊ ሂደት ሲገባ አይታይም።

ዘርፈ-ብዙ መፍትሄ

በቅራኔ እየከረረ ያለው ፓለቲካዊ ውጥረታችንን ማርገብ የምንችለው የቅራኔው መንስኤዎች ላይ በማተኮር ፥ ተግባራዊና አስታራቂ መፍትሄ በመወጠን ነው። ይሄንን ለማድረግ የሌሎች አገሮችን ተሞከሮ በአርአያነት በመጠቀም  የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ቅራኔ ምንጮች ማድርቅ እንችላለን።

ይሄን ለማድረግ የኔልሰን ማንዴላ መንግስት የወሰደውን ቀመር/ፎርሙላ መጠቀሙ አማራጭ የሌለው ሆኖ አግኘቼዋለሁ። ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ ነጮች መንግስት በጥቁሮችና በሌሎች ዘሮች ላይ ያደረገውን ግፍና እልቂት በጥበብና  አርቆ አስተዋይነት አርግቦታል።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በእጅጉ የተለያዬ ፓለቲካዊ ሁኔታዎች ላይ ያሉ ቢሆንም፥  የማንዴላ ቀመር የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ውጥረት ለማርገብ ፍቱን መድሃኒት መሆኑን አምንበታለሁ። ላብራራ።

የማንዴላ ቀመር/ፎርሙላ፦ እውነታ + እውቅና + ፍትህ = እርቅ

የማንዴላ መንግስት የውጥረት ማርገብ ስራውን የጀመረው እውነታን በማፈላለግ ስራ ነው። ቀጥሎም በተሰበሰበው መረጃ ላይ እውቅና የመስጠት ስራ ተካሄደ። የእውቅና ሂደቱን በቴሌቪዥን የተከታተላችሁ እንደምታስታውሱት በጣም ልብ ይሚነካ ሂደት ነበር። በመጨረሻም እውነታ ማፈላለጉና እውቅና የመስጠቱ ስራ ወደ ፍትህ አመራ።

የፍትህ ሂደቱ አንዳንድ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መንግስት ተሳታፊዎችን ከክስ ነጻ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ የሆነው በእውነታና በእውቅና ሂደት ውስጥ ስለተሳተፉና ለፈጸሙት በደል ይቅርታ ሰለጠየቁ ፡  እንዲሁም ያንን በማድረጋቸው የማንዴላ መንግስት ለተሳታፊዎቹ ከሰጣቸው ዋስትና የተነሳ ነበር። ለተበዳዮችና ቤተሰቦቻቸውም የደቡብ አፍሪካ መንግስት የገንዘብ ካሳ ከፍሏል። ውጥረትን ማርገብ ማለት ይህ ነው።

የእርቅ ሂደት ውጥረትን ያረግባል ፡ ለመግባባት ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።

እውነታ + እውቅና + ፍትህ = እርቅ!

*********

ያዬ አበበ የ65Percent.org መስራች ነው። የ65ፐርሰንት ድረ-ገጽ ግብ ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት የመሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

ተልዕኳችን | Our Mission

“65 ፐርሰንት” ትርጉም? የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ተልዕኳችን ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው። ግባችን ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

What is “65 percent”? 65% of Ethiopia’s population is under 24 years old. Our mission is to model a culture of political concensus for the 65%. Our goal is to advocate for, and initiate reconciliation and consensus among Ethiopians.

Post Archive