Aug 31, 2013

የእርቅ ማኒፌስቶ፦ ወደ ዲሞክራሲ የሚያደርስ አማራጭ መንገድ (ዶ/ር ዘለዓለም እሸቴ ይመር)

ያለፉት 23 አመታት በመንግስትና ተቃዋሚ መካከል ያለው ቅራኔ መፍትኤ አላመጣም። በጦርነት ስልጣን የያዘ መንግስት ዲሞክራሲ ይኸሁላችው ብሎ ይሰጥ ዘንድ አይቻለውም። በጦርነት መንግስት ለመቀየር የሚታገለውም ስልጣኑን ሲይዝ ከዚህ የተለየ አያደርግም። ኢትዮጵያ መውጫ ቀዳዳ ያጣች ትመስላለች። እሺ ብንል እርቅና መግባባት ዲሞክራሲን ለመውለድ ብቸኛ መንገድ ነው። እንዴት ማለት ጥሩ ነው። ሁላችንም የምንጠለልባት፦ በፍቅር ተሳስረን የምንኖርባትን ቤተ ኢትዮጵያን እንዴት እንገንባት?

1ኛ/ ሰላምን ብቻ መምረጥ ላይ መድረስ፦ የቤተ ኢትዮጵያ መሰረት።

የስላሙን ትግል ከትግሎች ውስጥ እንደ አንዱ ሳይሆን እንደ ብቸኛ አማራጭ መውሰድ ይገባል። ኢትዮጵያ ለዚህ አይነት ሰላም ራሳቸውን የሰጡ ሰላማዊ ተቃዋሚ ልጆች አላት። ሰላምን ብቻ መምረጥ ወደ ዲሞክራሲ የሚያደርሰው የእርቅና መግባባት አስተሳሰብ መሰረት ነው። ያለዚህ የመጀመሪያ እርምጃ ንቅንቅ ማለት አይቻልም። በሌላው በኩል ይህ ብቻ በራሱ ዋጋ የለውም። በዚህ መሰረት ላይ መሰራት ያለበት ምሶሶ ያስፈልጋል። ያም ምሶሶ መተማመን ነው።

2ኛ/ መተማመን ላይ መድረስ፦ የቤተ ኢትዮጵያ ምሶሶ።

መንግስት ለሰላም ትግል ነፃነት ሰጥቻለሁ ማለት ብቻ በራሱ ዋጋ የለውም። ተቃዋሚ የሰላም ትግል አካሄዳለው ማለቱ ብቻ በራሱ ትርጉም የለውም። መተማመን ላይ እስካልተደረሰ ድረስ ሁለቱም ውጤት አያመጡም። ለመተማመን ደግሞ ቃል በስራ መተርጎም አለበት። ለምሳሌ መንግስት የሕዝብን ሚዲያዎች በሙሉ ለራሱ መገልገያ ማዋል ብቻ ሳይሆን ለሰላማዊ ተቃዋሚ መድረኩን መክፈት ይጠበቅበታል። ያለበለዚያ እግርን ጥፍር አድርጎ አስሮ ሲያበቃ ለመሮጥ ነፃነት ሰጥቻለሁ እንደማለት ይቆጠራል። በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚው የሰላም ትግልን ከመረጠ የመንግስት ተቃዋሚ ብቻ ሳይሆን የትጥቅ ትግል የመረጡትንም ጭምር መቃወም ይጠበቅበታል። ያለበለዚያ በሁለት ቢላዋ ለመብላት እንደ መሞከር ይቆጠራል።

3ኛ/ መደማመጥ ላይ መድረስ፦ የቤተ ኢትዮጵያ ግድግዳ።

መተማመን ከተጀመረ መደማመጥ መከተል ያስፈልገዋል። ያለበለዚያ ምሶሶ ብቻ ታቅፎ ቤት አለን አይባልም። አንዱ ሌላኛውን ከጨዋታ አውጥቶ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ከመፈለግ ይልቅ በእርቅና በመግባባት የኢትዮጵያን ችግር አብሮ ለመቅረፍ መጣር ያስፈልጋል። ሰላማዊ ተቃዋሚ መሆን ጥቅሙ በጉልህ ይታይ። መንግስት ከሰላማዊው ተቃዋሚ ጋር በመጎራበት ሲሰራ ያየ ሁሉ የትጥቅ ትግል ጊዜ ያለፈበት ያረጀና ያከተመለት መሆኑን በሚገባ ይረዳል። ቤተ ኢትዮጵያም መልክ እየያዘ ይመጣል። ግን ጉዞው ገና ነው። ቤቱ መጠለያ ለመሆን ጣሪያ ያስፈልገዋል።

4ኛ/ ዲሞክራሲን ማዳበር ላይ መድረስ፦ የቤተ ኢትዮጵያ ጣሪያ።

ምሶሶና ግድግዳ ሳይቆም ጣሪያ መስራት እንደማይቻል ሁሉ፤ ዲሞክራሲን ለማዳበር ከዚህ በፊት የተዘረዘሩትን ከቁም ነገር ማስገባትና በስራ መተግበር ያስፈልጋል። መንግስትና ሰላማዊ ተቃዋሚዎች በመጎራበት ሲሰሩ፦ መንግስትና የትጥቅ ታጋዮች ጡንቻቸውን መጠቀም ሲተው ያኔ ዲሞክራሲ ለማደግ ፋታ ያገኛል። ይህ አማራጭ መንገድ የኛው በኛው ለኛው የሆነ የእርቅና መግባባት ስሌት ነው። ከሌላ ኮርጀን የምናመጣው አይደለም። እንግዲህ መንግስትና ተቃዋሚ አንዱ ያለሌላኛው ለኢትዮጵያ ዜሮ መሆኑን ይረዳ። መንግስትም ንቀቱን ይተው። ተቃዋሚም ጥላቻውን ይተው። ሁለቱም በእርቅና በመግባባት የኢትዮጵያን ውስብስብ ችግር ዲሞክራሲን በማዳበር ለመፍታት ይጣሩ። አዲስ አቅጣጫ ያስፈልገናል። ያለበለዚያ ያንኑ ያረጀ አካሄድ ይዘን አዲስ ምዕራፍ መሻገር አይቻልም። ኢትዮጵያ እንዲታደጓት የምትጠራው ሁለቱም ጎራ ውስጥ ያሉትን ልጆቿን ነው። የእናት ኢትዮጵያን ድምፅ የሚሰማ ይታጣ?


እባክዎን ስለ ብሔራዊ እርቅና መግባባት የተዘጋጀውን የሃሳብ ዳሰሳ (survey)፤ ለዚሁ አገልግሎት ወደ ተዘጋጀው ድህረ ገፅ በመሄድ ድምፅዎን ያሰሙ (እዚህ ላይ ይጫኑ)። ለሌሎችም ይሞሉ ዘንድ ያሳስቡ። አዲሱ አመት የእርቅና የመግባባት ዘመን ይሁንልን። የኢትዮጵያ ጉዳይ ግራ የገባው ሁሉ እጁን ወደ እግዚአብሔር ይዘርጋ፦ ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ እርሱ ፈጣሪያችን ኢትዮጵያን ይታደጋት!አይዞን እግዚአብሔር አለ።

ተልዕኳችን | Our Mission

“65 ፐርሰንት” ትርጉም? የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ተልዕኳችን ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው። ግባችን ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

What is “65 percent”? 65% of Ethiopia’s population is under 24 years old. Our mission is to model a culture of political concensus for the 65%. Our goal is to advocate for, and initiate reconciliation and consensus among Ethiopians.

Post Archive