Feb 5, 2014

የብሔራዊ እርቅ ጥያቄና ንቅናቄው በኢትዮጵያ - በሙሉአለም ገብረመድህን

ለብሔራዊ እርቅ ጥያቄ መታመን ወደ አተገባበሩ ይገፋል!
በዚህ አጀንዳ ለዓመታት ሲነሳና ሲወድቅ የነበረው የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ በገዥው-ግንባር በኩል አውንታዊ ምላሽ እንዲሰጠው የሚያስችል ንቅናቄ መፍጠር ስለሚቻልበት ሁኔታ ለውይይት መነሻ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ ጥቂት ሐሳቦችን ለመሰንዘር እና የብሄራዊ እርቅ ጥያቄው በተደራጀ ህዝባዊ ንቅናቄ እንዴት መመራት እንዳለበት፣ እነማን ቢመሩት የተሻለ ይሆናል በሚሉ ጉዳዮች የሚለውን የግል ምልከታዬን ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ በዚህ ፅሁፍ የተካተቱ የንቅናቄው ሐሳቦችና ለብሄራዊ እርቅ ጥያቄው መታመን እስከቻልን ድረስ ወደ አተገባበሩ እንደሚመሩን ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡
ያልተመለሰው የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ!
የ1966ቱን አብዮት በመጥለፍ ወደ ስልጣን የመጣው ደርግ፤ መንበረ-ስልጣኑን ለማፅናት ሲል በሄደበት የአገዛዝ መንገድ እጅግ ቁጥራቸው የበዛ ውድ የአገሪቱን ልጆች ህይወት ቀጥፏል፡፡ ዛሬም ድረስ ቂሙ ያልሻረ የስነ-ልቦና ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡  ደርግ መንግስታዊ ፍጅቱን እንዲያቆምና ብሄራዊ እርቅ እንዲያወርድ በጊዜው በነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ጥያቄ ቢቀርብለትም ‹‹እርቅ የሚባለውን የባልና ሚስት ጠብ አደረጋችሁት እንዴ?›› በማለት ከማገላበጥ በዘለለ አውንታዊ ምላሽ መስጠት ያልተቻለው የጁንታው ስርዓት የውድቀቱን ቀን በገዛ እጁ እዳፋጠነው የዘመነ-ደርግ ትርክት ያስረግጣል፡፡
ፍትሃዊ ማህበረሰብ እና ፖለቲካዊ ስርዓት ለመገንት የታገሉ ውድ የአገሪቱን ልጆች ቀጥፎ ካለፈው አገዛዝ በስም እንጂ በግብር የማይለየው ኢህአዴግ እየሄደበት ካለው የአገዛዝ መንፈስ የተነሳ ከመንግስታዊ ፍጅት እስከ ጅምላ እስር፣ ከብሄር ቅራኔ እስከ ጎሳ ግጭት፣ ከመንግስታዊ ሽፍትነት እስከ መንግስታዊ ሌብነት፣… ድረስ ያሉ ጥፋቶችን ያለ እርምት በተደጋጋሚ ያሳየ በመሆኑ ቁጥራቸው የበዛ አገር ወዳድ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የሲቪክ ማህበራት መንግስት የብሄራዊ እርቅ ጥሪ እንዲያደርግ ደግመው ደጋግመው ቢጠይቁም አገዛዙ ጥልቅ ተሸናፊ ከሆነው ደርግ በተለየ መልኩ ለብሄራዊ እርቅ ጥያቄው በጎ ምላሽ መስጠት ተስኖታል፡፡ ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት ውስጥ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የእርቅና ሰላም እድሎች መክነዋል፣ ጥያቄው ሲቀርብለት ‹‹ማን ከማን የተጣላ ኖሮ ነው እርቅ የሚያስፈልገው›› የሚለው ምፀታዊ ንግግር ከገዥዎቻችን አንደበት ዛሬም ድረስ ይደመጣል፡፡ የትላንት ጥፋቶች ግን ዛሬም ድረስ ቅርፃቸውን አንጂ ይዘታቸውን ሳይቀይሩ እንደቀጠሉ ነው፡፡ የአገሪቱ የጥፋት አዙሪት ዛሬም ከሽክርክሪቱ ሊወጣ አልተቻለውም፡፡ ዛሬም እንደ ትላንቱ በደል የማንነት አካል ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ትግልን በህገ መንግስታዊ ክበብ ስር ብቻ ለመተርጎም የመጫወቻ ሜዳው ጠቧል በሚል ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎች ቁጥር አስራ አንድ ያህል እንደደረሱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በህገ-መንግስቱ ጥላ ስር ያሉት ተቃዋሚ ፖርቲዎች አገዛዙ የመጣበትን የስልጣን መንገድ የመረጡ ኃይሎችን  ከማውገዝ ይልቅ ‹ለዚህ ውሳኔ የገፋቸው ራሱ ኢህአዴግ ነው› በሚል ጣታቸውን ገዥው ግንባር ላይ ከመቀሰር ወደኋላ ሲሉ አይታይም፡፡ ግንባሩ የሚያራምደውን የአገዛዝ መንፈስ ተከትሎ እስር፣ እንግልት፣ ስቅየትና ስደት በፖለቲካ ንፍቀ ክበብ ስር ያሉ ሰዎች የትግል መገለጫ ሆኗል፡፡ በገዥው ግንባር ስር ሁለት አስርታትን የተሻገረችው ኢትዮጵያ ዛሬም ድረስ የማህበረ-ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዋ በቅጡ አልተፈታም፤ ይህን ተከትሎ በአገሪቱ የፖለቲካ አደባባይ ላይ ‹‹አብዮታዊ ሁኔታ››ዎች እየታዩ ነው፡፡ አገሪቱን ከደም-ባህር መታደግ ይቻል ዘንድ አንድ ብቸኛ አማራጭ አለ፤ ብሔራዊ እርቅና ሰላም፡፡
የብሔራዊ እርቅ ጥያቄ በተበጣጠሰ መልኩም ቢሆን ዛሬም ድረስ ተስፋ ባልቆረጡ ወገኖች በኩል ይቀርባል፡፡ በዛኛው ጫፍ ያለው አገዛዝ ግን የተለመደውን ምላሽ ከመመለስ አልቦዘነም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፤ ኢህአዴግን ሊያስጨንቅ የሚችል የብሄራዊ እርቅ ጥያቄው በግዙፍ ህዝባዊ ንቅናቄ መታጀብ እስከ ቻለ ድረስ ግንባሩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር ላሉ የፖለቲካ ሃይሎች የብሔራዊ እርቅ ጥሪ ሊያደርግ ይችላል የሚል በጎ እምነት አለኝ፡፡ ቁም ነገሩ ለብሔራዊ እርቅ ጥያቄው መታመኑ ላይ ነው፡፡
ይህን ጥያቄ ወደ አደባባይ ገፍተው የሚያወጡ የንቅናቄው አራማጆችን እንደ አብነት በዚህ ፅሁፍ አካትቻቸዋለሁ፡፡ እነዚህን የንቅናቄውን አራማጅ ኃይሎች ለማነቃቃት፣ ሞራል ለመስጠት፣ በአቅም ግንባታ ስልጠና ለመደገፍ ምሁራን/ሙያዊ አበርክቷቸውን ያለስስት ሊሰጡ ይችላሉ ብዬ እንደ አርአያ-ሰብ ያጨኋቸው ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆችን በአዲስ ንዑስ ርዕስ እንዲህ ገልጫቸዋለሁ፡፡
የንቅናቄው መጋቢዎች
ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ፕ/ር ላጴሶ ጌልዴቦ፣ ፕ/ር ጌታቸው ሽፈራው፣ ዶ/ር እንድሪስ ሙሐሙድ፣ ልጅ ዳንኤል ጆቴ   (የኢት.አባት አርበኞች ማ/ር የወቅቱ ፕሬዘዳንት)፣ አቶ ቡልቻ ደምቅሳ፣ አምሳደር ዘውዴ ረታ፣ ወ/ሮ ማዕዛ አሸናፊ (የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ፕሬዘዳንት የነበሩ)፣ ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን (የቀድሞው የንግድ ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዘዳንት)፣ ጋዜጠኛ ማዕዛ ብሩ፣ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ ኡስታዝ ሐሰን ታጁ፣ አርቲስት ሙሃሙድ አህመድ (በነገራችን ላይ እነኝህ ምሁራን እና ታዋቂ ግለሰቦች እንደማሳያ የተጠቀሱ ናቸው)
የሃገረ-ኢትዮጵያ የእውቀት አደባባይ በዝምታ እንደተዋጠ፣ እጅግ ብዙዎቹ ምሁራን ከህዝባዊ ተዋፅኦ እንዳፈገፈጉ፣ ጥቂት የማይባሉ ምሁራን ደግሞ ከስርዓቱ ጋር በጥቅመኝነት የተሳሰሩ እንደሆነ አይካድም፡፡ እነዚኞቹ ግን አንድም አካዳሚያዊ አቅማቸውና አገራዊ አበርክቷቸው ሁለትም ያላቸው ህዝባዊ ተቀባይነትና ተደማጭነት በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ምሁራኑ የሚወክሉት የህብረተሰብ ክፍል ያለ በመሆኑ የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ ንቅናቄውን በተደራጀና በተጠና መልኩ ለመጀመር እንዲያስችል ለንቅናቄው አራማጆች ተገቢውን ድጋፍ ቢሰጡ፣ ምሁራንን በመቀስቀስ የማነሳሳት ስራ ቢሰሩ፣ ባለ ሀብቶች ይህን የተቀደሰ አላማ በገንዘብ እንዲደግፉ ቢያበረታቱ፣ ህዝቡ የንቅናቄው ተሳታፊ እንዲሆን በየተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ/ተቋም ቢቀሰቅሱ፣… የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ ንቅናቄውን ወደ አደባባይ ገፍቶ ለማውጣትና ገቢራዊ ለማድረግ ተኪ የሌለው አይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል የሚለው እምነት የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ነው፡፡
እርግጥ ነው! የንቅናቄው መጋቢ ይሆናሉ በሚል ካጨኋቸው ምሁራን ውስጥ የተወሰኑት በአገዛዙ እስርና እንግልት የደረሰባቸው የተገፉ ሰዎች ቢሆኑም፤ ይህ ንቅናቄ በደልን በመርሳትና ይቅር በማለት መጀመር ያለበት በመሆኑ፣ ተበዳዮቹ የምህረት ፍቅራቸውን ለአገዛዙ በማሳየት ስራቸውን ቢጀምሩ ለትውልዱ ትልቅ ትምህርት ይሆናል፡፡
የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ ንቅናቄው አራማጆች
  1. የሲቪክ ማህበራት ሚና፡- በ2001 ዓ.ም የፀደቀውን የበጎ አድራት ማህበራት አዋጅ ተከትሎ የሲቪክ ማህበራት ቁጥር እንደተመናመነ በተለይም በአገር አቀፍ ጉዳዮች እና ፖለቲካ ነክ በሆኑ አጀንዳዎች ዙሪያ የሚሰሩ ማህበራት ጭራሹን እየጠፉ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይሁንና አገር ቤት ባሉ አገር ወዳድ ምሁራን፣ ባለ ሃብቶች፣ በጎ አድራጊ ግለሰቦች በኩል  የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ እስከተደረገላቸው ድረስ እንደ ሰ.መ.ጉ፣ የባለራዕይ  ወጣቶች ማህበር፣ የመግባባት አንድነትና ሰላም ማህበር ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉት የሲቪክ ማህበራት ለዚህ አገራዊ ርዕይ ስኬት የመታመን እድላቸው ሰፊ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
እነኝህ ማህበራት፤ ምንም እንኳ ዛሬ ላይ በገንዘብ እጥረት የተነሳ በየ ክልል ከተሞች ቅ/ፅ/ቤቶችን በመክፈት ተደራሽነታቸውን ማስፋፋት እንዳልቻሉ ቢታወቅም፤ የንቅናቄው መጋቢ በሚል የተጠቀሱ ምሁራን ዘመኑን ሊያነፃ ለሚችለው ለዚህ ክቡድ ርዕይ ስኬት ሲባል ከማህበራቱ ጎን በመቆም ድጋፋቸውን የሚያሳዩ ከሆነ፤ እነኚህ ማህበራት እግረ ሙቅ የሆነባቸውን የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ ተቋቁመው ዛሬም ድረስ የማህበር ህልውናቸውን ማስቀጠል የቻሉ ናቸውና የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ ንቅናቄው ወደ አደባባይ እንዲወጣና ግቡ እንዲመታ የማድረግ እድል ይኖራቸዋል፡፡
ሲቪክ ማህበራቱ በንቅናቄው ጎዳና…
ከላይ ለማሳያነት የጠቀስኳቸው ሲቪክ ማህበራትና ሌሎችም በጋራ ትብብር የሚመሩት፤ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ‹‹የአገር ሽማግሌዎች የጋራ ምክር ቤት›› ማቋቋም የማህበራቱ ተቀዳሚ ተግባር ይሆናል፡፡
በዚህ የጋራ ምክር ቤት መቀመጫ ወንበር የሚኖራቸው አካላት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል፣ የሙያ ማህራት፣ የእምነት ተቋማት፣… የሚወክል መሆን ይኖርበታል፡፡ (በነገራችን ላይ የም/ቤቱ አባላት ዋነኛ ተልዕኮ መንግስት የብሔራዊ እርቅ ጥሪ እንዲያደርግ ማሳመን፣ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችና አገሪቱን ይወክላሉ የሚባሉ ሊሂቃን (Elites) የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው የውይይቱ ተሳታፊ እንደሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደመሆኑ መጠን የም/ቤቱ ወንበር የግድ የብሔር ተዋፅኦን መጠበቅ አይጠበቅበትም፡፡ ‹ኢትዮጵያ እንዴት ትበየን?› የሚለው ጉዳይ የእርቅና ሰላም ጉባኤው ተሳታፊ አካላት የሚወስኑት ይሆናል)
በእነ ፕ/ር ይስሃቅ የሚመራው ‹‹የአገር ሽማግሌ›› ቡድን በእውን ከመንግስት ያልተጣበቀ ስለመሆኑ የሚያሳይበት የቁርጥ ቀን/ጊዜ ይህ ይመስላል፡፡ በእርግጥም የአገር ሽማግሌው ቡድን በፖለቲካ ኃይሎች መሀከል ያሉ ቅራኔዎችንና ቁርሾዎችን ለማብረድ ብሎም እርቀ ሰላም ለማስፈን እየተጋ ያለ ከሆነ የድጋፍ ይሁንታውን በአዲስ መልክ ለሚቋቋመው የአገረ ሽማግሌዎች የጋራ ምክር ቤት በመስጠት አብሮ መስራት የሚችልበትን ሁኔታ የሚያመቻች ይሆናል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ መንግስትን ጨምሮ ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች (በሰላማዊም በትጥቅ ትግልም ከሚታገሉት፣ በአገር ውስጥም በውጭም ካሉት) ጋር የሚመክር ይሆናል፡፡ ም/ቤቱ ሌሎች የብሔራዊ እርቅ ንቅናቄው አራማጆች  የሚሰሯቸውን ስራዎች በተዋረድ የሚከታተል ቢሆን ይመረጣል፡፡ ሁሉም የንቅናቄው አራማጆች ዋነኛ አላማ በአገሪቱ ላይ ያንዣበበው ‹‹አቢዮታዊ ሁኔታ›› ወደ አልተጠበቀ ህዝባዊ አመፅ ከመቀየሩ  በፊት አገሪቱ በብሔራዊ  እርቅ እንድንነፃ ማድረግ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ንቅናቄ ውስጥ ተዋረዳዊና የጎንዮሽ ግንኙነት ቢኖር ተናቦ ለመስራትም ሆነ ለሚፈለገው ግብ ተመራጭ አካሄድ ይመስለኛል፡፡

ሲቪክ ማህበራቱ የጋራ ምክር ቤቱን ትርጉም ባለው መልኩ ከማንቀሳቀስ አኳያ ቀዳሚ ኃይል የመሆናቸው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የብሄራዊ እርቅ ንቅናቄው አካቶነት ያለው እንዲሆን ከማስቻል አኳያ በክልል ከተሞች እየተዘዋወሩ ብሔራዊ እርቅን ባስመለከተ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማካሄድ፣ ሴሚናሮችን ማዘጋጀት፣ በብሄራዊ እርቁ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የጥናት ውጤቶች በምሁራን ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ ህዝባዊ መድረኮችን ማመቻቸት፣ ለብሄራዊ እርቅ ንቅናቄው ድጋፍ የሚያደርጉ አጋር የሲቪክ ማህበራት (የውጭ አገራት) በኢትዮጵያ ባይኖሩም እንኳ በያሉበት ቦታ አለም አቀፉን ማህበረሰብ እንዲያነቃቁ ጥሪ ማስተላለፍ፣… በጥቅሉ  የብሄራዊ እርቅ ንቅናቄው ዋነኛ አራማጅ ሃይል የሲቪክ ማህበራቱ እንደ መሆናቸው መጠን፤ ለማንም የፖለቲካ ፓርቲ ባልወገነ መልኩ አገሪቱ ወደ ብሔራዊ እርቅና ሰላም የምታመራበትን ሁኔታ መፍጠር ተቀዳሚ ተግባራቸው ይሆናል፡፡
  1. የኃይማኖት ተቋማት ሚና፡- የብሄራዊ እርቅ ጥያቄውን ወደ አደባባይ ሊያወጡ ከሚችሉ የንቅናቄው አራማጅ ከሆኑ ተቋማት ውስጥ ዋነኞቹ የኃይማኖት ተቋማት ናቸው፡፡ ተቋማቱ በአገር ሽማግሌዎች  የጋራ ምክር ቤት ውስጥ ከሚኖራቸው አበርክቶ ባሻገር ‹‹በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ›› ስም ለገዥው ግንባር ከፍተኛ አመራሮች በአገሪቱ ውስጥ እርቀ ሰላም እንዲወርድ ጥሪ ማስተላለፍ፣ ለእርቀ ሰላም ጥያቄው አውንታዊ ምላሽ እስከ ሚሰጥ ድረስ በቤተ ክርስቲያናት ‹ምህላ›፣ በመስጅዶች ደግሞ ‹ቁነት/ልዩ-ፀሎት› ማዘጋጀት፣ የክርስትና ዘማሪያን፣ የእስልምና መንዙማ ባዮች/ማዲህ/ እንደየ ኃይማኖታቸው እርቀ-ሰላም ላይ የሚያተኩሩ መንፈሳዊ ስራዎችን በተናጠልና በህብረ-ዝማሬ መልኩ በሲዲና በካሴት መስራት፣ በየ አምልኮ ቤቱ በኃይማኖት መምህራን/ኡስታዞች አማካኝነት እርቅና ሰላም፣ መግባባትና አብሮነት ላይ የሚያተኩሩ ምስባኮች ከመቸውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በየጉባኤው እንዲሰሙ፣ በየ እድር ጀመአውና ማህበራቱ ቅራኔ ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ኃይሎች እርቀ ሰላም እንዲያወርዱ የሚጫኑ/የሚያስገድዱ አጀንዳዎችን መፍጠር፣… ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ እጅግ የተጠኑ ኃይማኖታዊ አበርክቶዎችን ምዕመናኑን ባሳተፈ መልኩ ማካሄድ የኃይማኖት ተቋማት ሚና ይሆናል፡፡ ይህን ለመሰለው ተግባር እንደ ማህበረ ቅዱሳን ያሉ በኃይማኖት ተቋማት ስር የተደራጁ ማህበራት ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
  2. የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ሚና፡- በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አገራዊ አጀንዳዎችን ወደ ህዝብ አይንና ጆሮ ለማድረስም ሆነ ለተከታዩ ትውልድ ከማስተላፍ አኳያ ኪነጥበብ አበርክቶዋ ላቅ ያለ እንደነበር ያስታውሷል፡፡ ለዚህ የቀደመ ተሞክሮ መታመን እስከተቻለ ድረስ፤ ሰዓሊያን፣ ቀራፂያን ደራሲያንና ድምፃዊያን የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ ንቅናቄውን በጥበብ  መንገድ በመግራት ወደ አደባባዩ የማውጣት  ጥበባዊ ኃይል ይኖራቸዋል፡፡ ሰዓሊያንና ቀራፂያን የእርቅ መንፈስን የሚያንፀባርቁ ስራዎቻቸውን በመስራት በኢግዚቢሽን መልክ ለህዝብ እይታ እንዲያበቁ ማድረግ፣ ደራሲያኑ በበኩላቸው ንቅናቄውን በሚደግፍ መልኩ ተከታታይ የወግና የግጥም ስራቻቸውን በልዩ ፕሮግራም ወደ ህዝብ የማድረስ ስራ መስራት፣ ድምፃዊያን ደግሞ በአገር ፍቅርና አንድነት፣ እንዲሁም በብሄራዊ እርቅና ሰላም ዙሪያ የሚያተኩሩ ዜማዎችን በተናጠል እና በህብረት በመሆን በተለያዩ ቋንቋዎች መስራት፣ በዚህ መንፈስ የተቃኙ የሙዚቃ ድግሶችን (ኮንሰርቶችን)  በአገር ቤትና በውጭ አራት ማዘጋጀት፣… ከኪነጥበብ ሙያተኞቻችንና የሙያ ማህበራቶቻቸው የሚጠበቁ ጥበባዊ ስራዎች ይሆናሉ፡፡
  3. የሚዲያ ተቋማት ሚና፡- አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የደፋር ሃሳብ መንሸራሸሪያ የሆነው ብቸኛው መድረክ የግሉ የሚዲያ ዘርፍ ነው (የገዥው ፓርቲ የግራ ጥፍር የሆኑትን አያካትትም) የሚዲያ ተቋማት የአደባባይ ምክንያተኝነትና ህዝባዊ መነቃቃትን በመፍጠር ረገድ አይነተኛ ሚና አላቸው፡፡ በዚህ የንቅናቄ ክፍል፣፤ ሁለት ክንፎች ይኖራሉ፡፡ የመጀመሪያው ክንፍ የማህበራዊ ድህረ-ገጽ ሲሆን፤ በዚህ የንቅናቄ ክንፍ የብሄራዊ እርቅ ጥያቄውን ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ   ማስተዋወቅ በሚቻልበት መልኩ አልሞ መስራት ግድ ይላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለየ መልኩ ከፍተኛ ተነባቢነት እያገኙ የመጡት የአገር ቤቶቹ ‹‹ድምፃችን ይሰማ!›› ኢቢቢ ኤን፣ ኢትዮ ቢባል የመሳሰሉት ‹‹ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ!›› የሚለውን ጥያቄ ከፍ በማድረግ የብሄራዊ እርቅ ጥያቄውን ማስተባጋት ተቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ሁለተኛው የንቅናቄው ክንፍ ደግሞ የህትመት ሚዲያው ሲሆን፤ በብሔራዊ እርቅ አስፈላጊነት ዙሪያ የሚያተኩሩ ፅሁፎችን በርዕሰ አንቀፅ፣ በአብይ አጀንዳ፣ በልዩ ዳሰሳ፣ በሐተታዊ ትንታኔ፣… መልኩ ማዘጋጀት፣ ተከታታይ ልዩ እትሞችን ወደ አንባቢ ማድረስ፣ በብሄራዊ እርቅ ዙሪያ የሚያተኩሩ ቃለ መጠይቆችን ከምሁራን፣ ከፖለቲከኞች፣ ከሲቪክ ማህበራት፣… ጋር ማካሄድ እንዲሁም ‹ነፃ ሚዲያ የተረሱትን፣ የተገለገሉትን እና የተጨቆኑትን የማህረሰብ ክፍሎች ድምፅ ማሰማት እና ግፉአኑ በገዥዎቻችው ዝንጋታ የተነሳ ስለሚደርስባቸው በደል እየተከታተሉ ዘገባ መስራት ይጠበቅባቸዋል› ለሚለው የሙያው መርህ መታመን ንቅናቄውን ወደ አደባባይ ለማውጣት በአያሌው ይጠቅማል፡፡  


ተስፋ አለን!

የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ በህዝባዊ ድጋፍ የታጀበ እንዲሆን ይቻል ዘንድ ንቅናቄው በተደራጀ መልኩ መካሄድ አለበት፡፡ የንቅናቄው መጋቢ ምሁራን እና ታዋቂ ግለሰቦች ሐሳቡን በቡድንም ሆነ በተናጠል እየመከሩበት ሲቪክ ማህራቱንና ሌሎች የንቅናቄው አራማጆችን ማሳተፍ በሚቻልበት ሁኔታ መጀመሪያ የግል አስተያየታቸውን በፅሁፍም ሆነ በቃለ-መጠይቅ መልኩ ለውይይት በሚያመች ሁኔታ ሃሳባቸውን ወደ ሚዲያው እንደሚያወጡት ተስፋ አለኝ፣ የንቅናቄው መጋቢ ምሁራን ሲቪክ ማህበራቱን በዕውቀታቸው እንደሚደግፉ፣ በየሚሰሩበት ተቋማት/ድርጅት አጀንዳውን በማንሳት የውይይት መንፈስ እንደሚፈጥሩ እምነቴ ነው፡፡ አሁን ያሉን የሲቪክ ማህበራት የአንድ እጅ ጣት የማይሞሉ ቢሆንም የንቅናቄው መጋቢ ምሁራን  ድጋፍ እስካልተለያቸው፣ ባለ ሃብቶች እጃቸውን እስከዘረጉላቸው ድረስ ጥያቄውን ወደ አደባባይ ገፍተው እንደሚያወጡት ተስፈኛ እንሁን፡፡ 

የኃይማኖት ተቋማት የገዥው ግንባር የፖለቲካ ክንፍ ሁነዋል የሚል የአደባባይ ሐሜት ቢኖርም ስለ ሰማያዊ ህይወታቸው የታመኑ፣ በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ የኃይማኖት መሪዎች እዳሉን አንርሳ፣ ተተኪ ወጣቶችም ለህዝብ አይንና ጆሮ ቅርብ እንደሆኑ አንዘንጋ፤ የጥቂቶች ጥረት፣ ብዙሀኑን ማነቃነቁ አይቀርምና ለብሔራዊ እርቅ ጥያቄው እንታመን!! የምሁራን ዝምታ ከእንቅልፍ በከበደ አርምሞ ቢመሰልም የገዛ ፍላጎታቸውን ያሸነፉ የአደባባይ ምሁራን ስላሉን በእርሱ እንበረታታ፤ የእርቀ ሰላም ማዕቀፍ በማዘጋጀትም ሆነ ንቅናቄውን በምሁራዊ ተዋስኦ በማጀብ እንዲተጉ አደራ እንበል፡፡… 

መንግስትንና  ህዝቡን ከማቀራረብ ባለስልጣናትን ለግል ጥቅማቸው የሚቀርቡ፣ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን ከመጠየቅ ልጃገረዶችን ደግሞ ደጋግሞ መጎብኘት የሚቀናቸው በእድሜ የገፉ ‹‹አርቲስቶች›› ያሉን በመሆኑ የምናፍርላቸውን ያህል፣ ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው ጎምቱ አርቲስቶች መንፈሳቸው ከግፉአኑ ጋር ስለሆነ በንቅናቄው የፊት መስመር ተሰላፊዎቻችን ይሆናሉ፡፡ ሚዲያው ለዘመኑ ጣኦት በሰነዱ፣ በብሔር አጥር በታጠሩ፣ የመክሸፍ ጥልቅ ማሳያዎች በሆኑ ‹‹የሙታን ዲሞክራሲ›› አምላኪዎች እንደተወረረ ቀድመን የተረዳን ቢሆንም ለህዝብና ለሙያቸው የታመኑ፣ ከብሔር አጥር ተሻግረው ኢትዮጵያን ለዘላለም የሚያኖራትን መሰረት በሙያቸው መርህ ለመተርጎም የሚተጉ የሚዲያ ሰዎች አሉንና በእነርሱ ተስፋ አለን! 

ቀጣዩ ዘመን በአብርኆት ይገለጥ ዘንድ የብሔራዊ እርቅ ጥያቄ ንቅናቄው ክረምቱን በውይይትና በቀና የሀሳብ ሙግት እያብላላን በማቆየት መስከረምን ጠብቀን ወደ አደባባይ እንደምናወጣው ተስፋ አለኝ! ‹‹ተስፋ ማድረግ ሰው መሆን አይደል፡፡ ተስፋ አልቆርጥም›› (በአሉ ግርማ)

(የብሄራዊ እርቅ ጥያቄውን ወደ አተገባበር መግፋት በሚቻልበት ሁኔታ ተቃዋሚ ፓርዎች እና የዲያስፖራው ማ/ሰብ ሚና ምን መሆን አለበት የሚለውን ሃሳብ በተመለከተ ሳምንት እመለስበታለሁ)

ተልዕኳችን | Our Mission

“65 ፐርሰንት” ትርጉም? የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ተልዕኳችን ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው። ግባችን ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

What is “65 percent”? 65% of Ethiopia’s population is under 24 years old. Our mission is to model a culture of political concensus for the 65%. Our goal is to advocate for, and initiate reconciliation and consensus among Ethiopians.

Post Archive