Dec 3, 2013

የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄና ፈተናዎቹ በኢትዮጵያ (ክፍል 2) – በዳዊት ተሾመ

4. የብሔራዊ ዕርቅ ፈተናዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች


በኢትዮጵያ የብሔራዊ ዕርቅ ፈተናዎች የሚመነጩት ስለ ብሔራዊ ዕርቅ ባለን ግንዛቤና እኛ ከለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ለመቃኘት በምናደረገው ጥረት ውስጥ ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ብሔራዊ ዕርቅ ሲነሳ እንድ ዋነኛ መነጻጸሪያ ሁኖ የሚቀርበው በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተካሄደውን ብሔራዊ ዕርቅን ነው:: በአብዛኛው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የሚታሰበው የደቡብ አፍሪካ ዕርቅ ምንም እንከን እንደሌለውና በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም አንጻር ሊደገም እንደሚችል ነው:: ነገር ግን፣ የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ዕርቅ ሂደት የራሱ የሆኑ ጉድለቶች ያሉበት ከመሆኑም በላይ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ አንጻርም ብዙ ልዩነቶች አሉት:: ስለዚህም፣ በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ብሔራዊ ዕርቅ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን መሆን አለበት:: ከዚህ አንጻር በኢትዮጵያ የብሔራዊ ዕርቅ ፈተናዎችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንደሚከተለው ቀርቧል::

ሀ) እውቅና ስለመስጠትና የብሔራዊ ዕርቁ አካሄድ ላይ ያሉ ፈተናዎችና የመፍትሄ ሃሳቦች ላለፉት ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነቶችና በደሎች እውቅና መስጠት ላይ የሚታዩት ችግሮች ሁለት አይነት ናቸው:: አንደኛው ችግር ያለፉትን በደሎች እውቅና መስጠት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ ነው:: ይኸ ማለት ላለፉት በደሎች እውቅና መስጠት ማለት በደሎችን የፈጸሙ ኃይሎች ለፈጸሙት በደሎች ተጠያቂነት ስለሚያመጠና በደሉን ፈጽመዋል የሚባሉት ደግም እንደ <ሀገር-መስራች፣ ስልጣኔ አስተዋዋቂና ሰለምና ብልጽግና አምጪ> በሚል በተለምዷዊው የኢትዮጵያ ታሪክ (meanistream Ethiopian history) ተክለ-ሰውነታቸው ስለተሳለ ነው:: ሁለተኛው ችግር ያለፉት በደሎች ዕውቅና ቢሰጥ ቀጥሎ ሊመጣ የሚችለው ነገር ላይ ብዥታ መኖሩ ነው:: ይህም ማለት ዕውቅና ቢሰጥ ተበድለናል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ለራሳቸው ፖለቲካዊ ጥቅም ሊያውሉት ይችላሉ የሚል ፍራቻ መኖሩ ነው:: እነዚህ ዕውቅና በመስጠት ላይ ያሉ ተግዳሮቶች በምንም መልኩ በደሎችን በመካድ ሊፈቱ አይችሉም:: እንደ አቅጣጫ መወሰድ ያለበት አካሄድ ያለፉትን በደሎች አለመካድና በድጋሚ እንዳይፈጸሙ ማድረግን ነው::

በሌላ በኩል ደግሞ፣ በደሎቹ የተፈጸሙበት ወቅት ያለውን የአስተሳሰብ ደረጃና የአገዛዛ ባህሪ ከጭፍን ስሜታዊነት ውጭ መመልከት ተገቢ ነው:: ታሪክ ለፖለቲካዊ ግብ መምቻ ብቻ ከመጠቀም ወጥተን ታሪክን ለታሪክ ተመራማሪዎች መተውን መልመድ መቻል አለብን:: በሀገራችን ሊኖረን የሚገባው ፖለቲካ ትላንትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን በነገው ብሩህ ቀንና አብሮነታችን ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል:: ይህ ማለት፣ ሙሉ ለሙሉ ታሪክን ከፖለቲካ መነጥል ይቻላል ማለት አይደለም:: ይልቁኑም ፖለቲካችን በባለፈው ታሪካችንና በነገው አብሮነታችን እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታችን ላይ ያለውን ሚዛን ማስተካከል ቁልፍ መሳሪያ መሆን ይገባዋል::

በአገራችን የነበሩ አገዛዞች ምንም እንኳን ማህበረሰባዊ መሰረታቸውን በስነ-ልቦና ደረጃ ተጠቃሚ ያደረጉ ቢመስልም፣ በሁሉም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ህዝቦች በባለፉት አገዛዞች ተበዳዮች ናቸው፤ የበደላቸው መጠንና የበደላቸው አይነት ምንም እንኳን ቢለያዩም:: ያለፉት አገዛዞችም ሆነ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የጠቀሙት ጥቂት ከስርአቱ ጋር ቅርበት ያላቸው ልሂቃንን እንጂ በአጠቃላይ ልሂቃኑ የወጡበትን ወይም እንወክለዋለን የሚሉትን ማህበረሰብ አይደለም:: ስዚህም፣ ያለፉትን በደሎች ዕውቅና መስጠት ማለት ይህ ህዝብ በዚህ ህዝብ ተበድሏል፤ እከሌ የሚባል ህዝብ በዳይ እከሌ የሚባል ህዝብ ተጎጂ በሚል መንፈስ መሆን የለበትም:: ሁሉም ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነቶችም ሆነ በደሎች መታየት ያለባቸው በደሎቹን የፈጸሙት አገዛዞች ከተመሰረቱበት ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረቶች የመነጩ መሆናቸውን ነው::

ይህ አካሄድ አንድ በኩል በህዝቦች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን በቂም በቀል የታጀለ ማህበረሰባዊ ግንኙነት መሰረት እንዳይዝ ሲያረግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከባለፈው ታሪካችን ተምረን የተሻለ ነገን ለመፍጠር ለምናደርገው ሂደት ማህበረሰባዊ መነቃቃትን ይፈጥርልናል:: ስለዚህም፣ በዚህ አካሄድ ላለፉት በደሎች ዕውቅና በመስጠት ሊከሰት የሚችለው የፖለቲካ ኃይሎች ያለፉትን በደሎች ፖለቲካዊ ትርጉም በመስጠት ለፖለቲካ ጥቅም የሚያውሉበትን እድል ማጥበብ ይቻላል:: በመሆኑም፣ የብሄራዊ እርቅ ጉዳይ መታየት ያለበት የባለፈውን ጠበሳ በመነካከት ቅራኔን በማባባስ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማስገኘት ሳይሆን ከባለፈው ታሪክ በመማርና ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነትን በማረም የተሻለ ነገንና ብሩህ-ተስፋን ከመፍጠር አንጻር መሆን ይገባዋል::

ለ) የተፈጸሙትን በደሎች ያስከተሉት ውጤቶች ላይ፣ ተጎጂዎች የከፈሉት መስዋትነት እና እንድምታ ላይ ስምምነት መድረስን (Consensus building) በተመለከተ ያሉ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር <ብሔራዊ ዕርቅ የሚያስፈልገው ለየትኛው ታሪካዊ በደል ነው> የሚለው ጥያቄ በተፈጸሙ በደሎች ላይ ስምምነት ለመድረስ ወሳኝ ጥያቄ ነው:: ኢትዮጵያ የአሁኗን ቅርጽ እንድትይዝ ካደረጋት የሀገር ግንባታ ሂደት አንስቶ አሁን እስከምንገኝበት ዘመን ውስጥ የተፈጠሩትን ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነትና በደሎችን ማካተት አለበት:: እነዚህን ሁሉ በደሎች አንድ ሰው ወይም አንድ አገዛዝ ሳይሆነ የፈጸመው፣ በየወቅቱ በሀገራችን የሰፈኑት አገዛዛችና አገዛዛቹን የመሰረቱት እና ተጠቃሚ በሆኑት ለአገዛዛቹ ቅርበት ባላቸው ጥቂት ልሂቃን ነው:: ስለዚህም፣ ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት የጎደላቸው ነገሮች ተደግረዋል፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገዛዛቹ ተበድለዋል፤ የበደሉ አይነትና መጠን ቢለያይም:: ስለዚህም የተፈጸሙት በደሎች ያስከተሏቸው ውጤቶች በደንብ ተመርምረው ለታሪክ መማሪያነት መቀመጥ አለባቸው:: እንደ ሁሉም ሀገር፣ ሀገራችን ኢትዮጵያም ያላት ታሪክ <ጥሩም መጥፎ> ነው:: ከ<ጥሩ> ታሪካችን አንድነታችንን የበለጠ በማጠናከር <ከመጥፎው> ታሪካችን ደግሞ በመማር ማህበራዊ ግንኙነታችንን ይበልጥ በመተማመንና በመከባበር ላይ የተመሰረት ማድረግ እንችላለን:: ስለዚህም፣ የተፈጸሙት በደሎች ያስከተሉት ውጤቶችና ተጎጂዎች የከፈሉት መስዋትነትና እንድምታ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ተመዝግቦ መያዝ ይገባዋል::

ለዚህም አላማ ሲባል ሊደረጉ የሚችሉ ተግባራት የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ:: አንደኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የነበሩና ያሉ ግንኙነቶች፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በአግባቡ ሳይንሳዊ መሆነ መንገድ ተጠንተው እንዲቀመጡ በየዩኒቨርስቲዎቻችንና መንግስታዊ በሆኑ የምርምር ተቋማት ውስጥ እንደ አንድ ፕሮግራም ተቀርጾ ሊዘረጋ ይችላል:: በዚህም ሂደት የብሔራዊ ዕርቁን ተቋማዊ ገጽታ ማላበስ ይቻላል:: ሁለተኛ፣ ብሄራዊ ዕርቁን የሚመለከት መታሰቢያ ብሄራዊ ቀን ቢመረጥና በየዓመቱ የምርምር ስራዎች የሚቀርቡበት፣ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር፣ በመከባበርና ፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በማህበረሰባችን ውስጥ ሊመጡ በሚችሉ ተግባራት ታስቢ እንዲውል ማድረግ ይቻላል:: ሶስተኛ፣ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በታሪካዊ በደሎች ምክንያት ውድ ህይወታቸውን ላጡ፣ ከመኖሪያቸውና ከአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ እና የተለያዩ መሰዋትነት የከፈሉትን ሰዎች ለማስታወስ ሃውልት እንዲቆም ማድረግ የሚቻል ነው::

ሐ) የተፈጸሙት በደሎች በድጋሚ እንዳይፈጸሙና የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎትና ደህንነት የሚያረግገጥ ስርአት ለመፍጠር መዋቅራዊ ለውጦችን ማምጣትና የፖለቲካ ውህደትን ማሳለጥን (Structural changes and institutionalization of the process of political integration)፣ ብሔራዊ ዕርቅ ማህበራዊ ለውጥን ለማማጣትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት እንደ ወሳኝ ግብአት የምንጠቀምበት ከሆነ፤ ብሔራዊ ዕርቅ ሂደት በራሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው:: ይህ ማለት የተፈጸሙት በደሎች በድጋሚ እንዳይፈጸሙና የተገለሉ የማህበረሰቦች ክፍሎች ፍላጎትና ደህንነት የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መፈጠር አለበት:: ይህን ለማድረግም፣ የፖለቲካ ስርአቱ የሚመራበትን የጨዋታ ህግ ማውጣትና የጨዋታውን ህግ የሚመሩ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት ይጠይቃል:: ይህም ማለት በማህበረሰባችን ውስጥ መዋቅራዊ ለውጦችን ማምጣትን የሚጠይቅ ነው:: የሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎቶችና ደህንነት ለማስከበር የፖለቲካዊ ስርአቱ ውስጥ ሁሉንም ተሳታፊ ማድረግ ግድ ነው::

ከዴሞክራሲያዊ ስርአት ውጪ በሀገራችን ያለውን ብዝሃነት ሊያስተናግድ የሚችል ስርአት የለም:: ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በመሰረቱ ሁለት ግቦች ላይ ማነጣጠር አለበት:: አንደኛ፣ በዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ሂደት ውስጥ ተቋማት የሚወክሉት ግለሰቦችን አሊያም የተወሰኑ የልሂቃን ቡድኖችን አይሆንም:: ተቋማት የሚወክሉት ስምምነት የተደረሰባቸውን የጨዋታ ህጎችን ሲሆን እነዚህም ህጎች በልሂቃን ውስጥ የሚፈጠሩ የጥቅምና የፍላጎት ግጭቶችን ለመዳኘት ዋና መሳሪያ ይሆናሉ:: ስለዚህም፣ የብሔራዊ ዕርቅ ሂደት ዴሞክራሲያዊ ተቋማትንና የጨዋታ ህጎችንና ደንቦችን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በሚስማሙበት መልኩ ለመቅረጽ የሚያስችል ሂደትን ይፈጥራል:: ይኸም ማለት ብሄራዊ ዕርቅ ከሚመጣባቸው ዋነኛ ሂደቶች መካከል የጨዋታ ህጎቹ የሚወጡበት አግባብና ሂደት ወሳኝ ነው:: ኢህአዴግ ብሔራዊ ዕርቅን የሚመለከትበት አግባብ ማለትም << ብሔራዊ ዕርቅ ማለት አሁን በለው ህገመንግስና ህገመንግስታዊ ስርአቱ ላይ መግባባት መፍጠር ነው::>> የራሱን ፖለቲካዊ የበላይነት ለማስጠበቅ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም:: ምክንያትቱም የጨዋታ ህጎቹ የወጡበት አግባብና ሂደት ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን ያገለለ ከመሆኑም በላይ ዋነኛ ተገዳዳሪ የሚባሉትን በተለይ ደግሞ ሀገር-አቀፍ ፖለቲካ የሚያራምዱትን ያላካተተ ነው::

ሁለተኛ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ስርአት የስልጣን ክፍፍልን ስለሚያመጣ፣ ተጠያቂነትን ስለሚያሰፍንና ፖለቲካዊ ስልጣን በጉልበት ሳይሆን በህዝብ ፍላጎት ላይ በተመሰረተ አካሄድ ስለሚያዝ አዲስ ፖለቲካዊ ባህልን በሃገራችን ውስጥ እንዲሰፍን ያደርጋል:: ስለዚህም፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ የስልጣን ክፍፍሎሽ ስለሚኖር በልሂቃኖች መካከል ሊኖር የሚችለው የስትራተጂና የታክቲክ ጉዳይ እንጂ ጫፍ የወጣ ፖለቲካዊ ልዩነት አይሆንም:: በመሆኑም የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ መዋቅራዊ ለውጥ ከማምጣትና ፖለቲካዊ ውህደትን ከማሳለጥ አንጻር መታየት ያለበት ነው:: ይኸም፣ ፖለቲካዊ ውህደት የጋራ ነገን ከመፍጠርና የጋራ ራዕይ እንዲኖረን እና አዲስ ሲቪክ ፖለቲካዊ ባህል እንዲገነባ ከማስቻሉም በላይ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መሰረት ይሆናል::

መ) ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት በማምጣት ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ማረጋገጥ (enhancing socio-economic development and economic integration)

በታሪካችን እንደምንመለከተው ከሆነ በአብዛኛው በልሂቆቻችን መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች በፖለቲካ ሃሳቦች ልዩነት ላይ የተመሰረቱ ሳይሆን አንዱ አንዱን ጥሎ በማለፍ የፖለቲካ ስልጣን ለመቆጣጠር በሚደረጉ ግብግቦች ላይ የተመሰረቱ ናቸው:: የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ በዋናነት የሚያያዘው ደግሞ የሀገሪቱን ሀብት ከመቆጣጠር ጋር ነው:: በግልጽ ለማስቀመጥ ያክል የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሀገር ምስረታ ሂደት ፖለቲካዊው እንድምታው ያልተማከለና በጣም ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት መመስረት ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊው እንድምታው ደግሞ በጦር አሸናፊ ሆነው የማዕከላዊ  መንግስት ምስረታን ሂደት የተቆጣጠሩትን ኃይሎች የኢኮኖሚ ጥቅሞችን የማስከበር ሂደት ነበር:: ይህ ሂደት በደርግ አገዛዛም ሆነ በኢህአዴግ አገዛዝ የተደገመ ነው:: በዘውዳዊው፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ አገዛዞች የተዘረጉት ኢኮኖሚያዊ ስርአቶች የሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚነት ያላረጋገጡና የአገዛዞቹን ቀጣይነት ብቻ ለማረጋገጥ ያለሙ ናቸው:: ይህም በመሆኑ የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ ኢኮኖሚያዊ ፍትሃዊነትንና የህዝብ ተጠቄሚነት ላይ ያነጣጠረ መሆን ይገባዋል::

እንደ ደቡብ አፍሪካ ፖለቲካዊ ስልጣን ላይ ብቻ የተመሰረት የብሄራዊ ዕርቅ ሂደት በኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ርቀት የማይወስድ ብቻ ሳይሆን ወደ በለጠ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የሚያጋልጥ ነው:: ስለዚህም የኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አንዱ የብሔራዊ ዕርቅ ዋና አላማ መሆን ይገባዋል:: በሌላ በኩል ደግሞ፣ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማረጋገጥ እና በክልሎች መካከል ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው:: ድህነት በራሱ ሰዎች በወደፊት ሕይወታቸው ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ፣ ጨለምተኛ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ ለዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂ የሚያረጉት አንድ ነገር ይፈልጋሉ፤እራስን ከጥፋተኝነት ነጻ ለማውጣት:: ስለዚህም ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነቶችን ለዛሬው ውድቀት ብቸኛ ተጠያቂ እንደሆኑ ሲታሰብ፣ በተወሰኑ ልሂቃን ደግም ይህን ስሜት ለራሳቸው ፖለቲካዊ ጥቅም እንዲውል ያደርጋሉ፣ እያደረጉም ነው:: ስለዚህም፣ ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማስፋን የብሔራዊ ዕርቅ ውጤታማነትንና ዘላቂነትን ከማረጋገጥ አንጻር ወሳኝ ነው::

ከዚህ ጎን ለጎን፣ ሙስናን ማስወገድ የሚያስችሉ ተቋማዊ፣ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ ሪፎርሞችን ማካሄድ ግድ የሚል ነው:: በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቁጥጥር ስር ያዋሉት ሶስት ኢኮኖሚያዊ ሃይላት ናቸው:: እነርሱም፣ መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቆጣጠራቸው ድርጅቶች፣ የሚድሮክ ድርጅቶች እና በኢፈርት ድርጅቶች ናቸው:: ይህም፣ የአሁን ኢኮኖሚ ስርአት በዋናነት የፖለቲካ ስልጣን የተቆጣጠሩት ጥቂት ልሂቃን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በቀጥታ የሚቆጣጠሩበትን አግባብ ተቋማዊ ገጽታ የሚያላብስ ነው:: ስለዚህም፣ ፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ከዚህ ልማት እኩል ተጠቃሚነትን ከማስፈን አንጻር ሙስናን ማስወገድና ተወዳዳሪነትን የተላበሰ ኢኮኖሚያዊ ስርአት መዘርጋትን ግድ የሚል ነው:: በሌላም በኩል፣ በባለፉት የአገዛዝ ስርአቶች ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ትሩፋት የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል:: ይኸም፣ በባለፉት አገዛዞች ተበድለናል የሚሉ የፖለቲካ ልሂቃን ጫፍ የወጣ የፖለቲካ አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ የሚስገድዳቸው፣ የማያስተካክሉ ከሆነ የማህበረሰባዊ መሰረታቸው እንዲያጡ የሚያደርግ፣ ከተናጥል ጉዞ የአብሮነት ጉዞ እንደሚበልጥ ሰፊው ህዝብ እንዲረዳ የሚደርግ ነው:: በመሆኑም፣ ይህ ሁኔታ የብሄራዊ ዕርቅ ዘላቂነትን ከማረጋገጡም በላይ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወሳኝ ነው::

ሠ) ለብሔራዊ ዕርቅ ምቹ ሁኔታን ስለመፍጠርና አማራጭ መፍትሄዎች

እስካሁን ድረስ ብሔራዊ ዕርቅን ለማሳካት ምቹ ሁኔታን አልተፈጠረም:: ይህ ምቹ ሁኔታ አለመኖር የሚመነጨው ከገዢው ፓርቲ ከፋፍሎ የመገዛዝ ባህል እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣዊ ደካማነትና የጋራ አላማ መፍጠር አለመቻላቸው ነው:: ብሔራዊ ዕርቅ እንዲሳካ ስልጣን ላይ ያሉ ገዢዎችን የሚያስገድድና የሚገዳደር ተቃዋሚ ኃይል መኖርን ግድ የሚል ነው:: ካለ ጠንካራ ተቃዋሚ ኃይል የሚገኝ ብሔራዊ ዕርቅ፣ ዕርቅ ሊባል የሚቻል አይደለም:: ምክንያቱም የዕርቅ ሂደቱ ስልጣን ላይ ያሉ ልሂቃንን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው፤ ሁሉን የፖለቲካና ማህበረሰባዊ ኃይላትን የሚያካትት አይደለም:: ከዚህ ቀደም በወጡ ጹሁፎቼ እንዳመለከትኩት፣ የኢትዮጵያ የተቃውሞ ኃይሎች በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉት በብዙ ችግሮች የተተበተቡ ናቸው:: የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄ ግማሹ ምላሽ በተቃውሞ ኃይላት ጥንካሬ ላይ የሚመሰረት ነው:: አንድነት ጥንካሬ፣ መከፋፈል ድክመትን እንደሚያመጣ ከባለፈው ታሪካችን በተሻለ ሁኔታ ልንማርበት የምንችልበት መድረክ የለም:: ስለዚህም፣ በተቋማዊ ብቃት፣ በስትራተጂ፣ በታክቲክ እና አባላትን በማፍራት ተቃዋሚ ሃይላት ከገዢው ፓርቲ ጋር ተገዳዳሪ መሆን አለባቸው::

አብዛኞቹ የሀገራችን የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸው ርዕዮተ አለማዊ፣ ስትራተጂያዊ ወይም ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በግለሰቦች ቁርሾ ላይ የተመሰረተ ነው:: ስለዚህም፣ ግለሰባዊ ቁርሾዎችን ከብሔራዊ ፖለቲካ ጥያቄ መለየት መቻል አለብን:: በሌላም በኩል፣ አሁን የሚታየው የፖለቲካ ኃይሎች መሰባሰብ ይበል የሚያስብል ሲሆን፣ እዚያው ሳለም ሁሉን ማህበረሰብ የሚያቅፍና የሚያንቀሳቅስ አጀንዳ መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል:: ተቃዋሚ ኃይላት ማህበረሰባዊ መሰረታቸውን መስፋትና ሁሉን የማህበረሰብ ክፍል (cross-cutting social cleavages) ማቀፍና ማንቀሳቀስ መቻል አለባቸው:: ይህን በማድረጋቸው፣ ገዢው ፓርቲ ስልጣን ላይ ብቻውን ለመቀመጥ የሚከፍለው መሰዋትነት በዕርቅ ሂደት ውስጥ በመሳተፍና ፖለቲካዊ ስርአት ለውጥ በመምጣቱ ከሚያጣው ጥቅም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እንዲሆን ያደርገዋል:: ይኸም፣ ለዘብተኛ የአገዛዙን ልሂቃን ወደ ብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄን እንዲያራምዱ ሲያስችላቸው፣ አክራሪ ልሂቃንን ደግሞ የበለጠ ደካማ ያረጋቸዋል::

በሌላ በኩል ደግሞ፣ የብሔራዊ ዕርቅ ስትራተጂያዊ ውጤቶችና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባት ሂደት ተጠቃሚዎች ጥቂት ልሂቃን መሆን የለባቸውም:: በብሔራዊ ዕርቁ ሂደት ማንም የፖለቲካ ኃይል ሳይሆን አሸናፊ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት፣ አንድነት እና ሉአላዊነት ነው:: ስለሆነም፣ የብሔራዊ ዕርቅ ሂደት ማነጣጠር ያለበት ማን ስልጣን ላይ ወጣ የሚለው ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ የጨዋታ ህጎች ማውጣት እና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት ላይ ነው:: ይኸም፣ የብሄራዊ ዕርቁ ስተራተጂያዊ ውጤቶች (ዴሞክራሲያዊ ስርአት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ሀገራዊ መግባባት) እና ታክቲካዊ ግቦች መካከል አንድነትንና ሚዛንን የሚያስጠብቅ ይሆናል:: በመሆኑም፣ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ለብሔራዊ ዕርቅ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም በላይ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወሳኝ ግብአት ነው::

5. ማጠቃለያ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በብዙ ውስብስብ ታሪካዊ ሂደት ያለፈች ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ ያሉብን ችግሮች መጠነ ሰፊና ውስብስብ ናቸው:: እስካሁን ድርስ ጉልበት ላይ የተመሰረተ ልዩነቶችን የመፍታት ሂደቶች የበለጥ ልዩነቶችን ውስብስብ እንዲያደርግና ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ስር እንዲሰድ ሆኗል:: ምንም እንኳን ከደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ውድቀት በኋላ የተለያዩ የብሔራዊ ዕርቅ አስተሳሰቦች በሙሁሯንና በፖለቲካ ኃይላት ቢራመዱም፣ የብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄን የፖለቲካ ኃይላት የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ማሳኪያ መሳሪያ ያደረጉበት አረዳድ እንደሰፈነ መረዳት አያዳግትም:: የብሔራዊ ዕርቅ ሂደት ውስብስብ ችግሮችን የምንፈታበት ሂደት እንደመሆኑ መጠን በእንዳንዱ ጥቃቅን በደሎች ላይ የምናተኩርበት፣ ፖለቲካዊ ትርፍ የምናሰላበት፣ አግላይ ስርአት የሚመሰረትበት ሂደት ሳይሆን የተሻለች ኢትዮጵያንና ብሩህ ቀን የመፍጠር ሂደት አካል መሆን ይገባዋል::

በዳዊት ተሾመ (dawit-teshome@hotmail.com)

ምንጭ፦ http://www.zehabesha.com/amharic/archives/10340

ተልዕኳችን | Our Mission

“65 ፐርሰንት” ትርጉም? የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ተልዕኳችን ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው። ግባችን ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

What is “65 percent”? 65% of Ethiopia’s population is under 24 years old. Our mission is to model a culture of political concensus for the 65%. Our goal is to advocate for, and initiate reconciliation and consensus among Ethiopians.

Post Archive