Feb 7, 2014

ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ለኢትዮጵያ ጥናታዊ ጽሁፍ - ተክሉ አባተ

 ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ለኢትዮጵያ: ጥናታዊ ጽሁፍ


 ተክሉ አባተ
በአገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ብሄር ገነን ሥርዓት በእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመተካት ኢትዮጵያውያን (የ አገር ዜግነት ያላቸውን ትውልደ ኢትዮጵያውያንንም ማለቴ ነው) የተለያዩ  መንገዶችንና ዘዴዎችን በመጠቀም እየታገሉ ይገኛሉ:: በአገር ቤት ያሉ ወደ 100 የሚጠጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በይፋ ሰላማዊ የትግል ስልት ይከተላሉ ቀላል የማይባል ህዝብም በሰላማዊ መንገድ መታገል እንደሚበጅ ያምናል:: በጣት የሚቆጠሩ ድርጅቶች ደግሞ እሾህን በእሾህ እንዲሉ መሳርያ አንስተው ወደበረሃ ገብተዋል:: እንደ ግንቦት 7 ያሉት ደግሞ ሁሉንም አይነት የትግል ስልት መጠቀም አዋጭ እንደሆነ ያምናሉ::

በአንድም በሌላም መንገድ ስለነዚህ የትግል ስልቶች አንጻራዊ አዋጭነትና አስፈላጊነት ውይይቶች ሲደረጉ ነበር:: ነገር ግን የትኛው የትግል ስልት ትክክለኛ ለውጥ ለማምጣት አስተማማኝ እንደሆነ መደምደም የሚቻል አይመስልም:: ለዚህም ይመስላል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያዎችና በድረ ገጾች የሚደረጉ ውይይቶችና የሚለቀቁ መጣጥፎች ይህን ጉዳይ በቀጥታ የማያነሱት::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርከት ያሉ ውይይቶችና መጣጥፎች እያተኮሩበት የመጣው ጉዳይ ትንሽ የተለዬ ይመስላል:: ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ማድረግ ለአገራችን ሰላማዊና ዘለቄታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል እየተነገረ ነው:: ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ማድረግ ከባህላችን ጋር አብሮ ከመሄዱም በላይ እጅግ አስፈላጊና ወቅታዊም እንደሆነ የሚሞግቱ አሉ:: በአንጻሩ ደግሞ ብሄራዊ እርቅ ፈጽሞ የማይሰራ ከመሆኑም በላይ የህግንና ፍትህን መርሆች የሚቃወም እንደሆነ የሚያስጠነቅቁም አሉ:: አንዳንዶች ደግሞ ስለብሄራዊ መግባባትና እርቅ ማውራትና መወያየት የዋህነት አላዋቂነት ሃይማኖታዊነት እንደሆነ በድፍረት ይናገራሉ:: ሌሎች ደግሞ ሃሳቡ መንግስትና ባለሥልጣናቱን ለመታደግ የታሰበ የቆረጣ ስልት እንደሆ ይጠቁማሉ::

ዳሩ ግን ብሄራዊ ኢትዮጵያዊ መግባባትና እርቅን በተመለከተ ጠቅለል ያለ የዳሰሳ ጥናት እስካሁን አልቀረበም:: ጉዳዩን በተመለከተ የሚደረጉት የተናጥል ውይይቶችና የተጻፉት መጣጥፎች የተሟላ ሃሳብ ለማግኘት አያስችሉም:: እንዲያውም በጉዳዩ ላይ ምን ያህል እንደተጻፈና ምን ምን ዝርዝር ሃሳቦች እንደተነሱ አይታወቅም:: ይህም ብሄራዊ መግባባትና እርቅ በይፋ እንደ አንድ የትግል ስልት እንዳይቆጠርና በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ዳብሮ ሥራ ላይ እንዳይውል ተጽእኖ  አሳድሯል:: ይህን ችግር ለመቅረፍ የዳሰሳ ጥናት አስፈላጊ ሆኗል:: የዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ ዓላማ ጉዳዩን በተመለከተ የተጻፉትን መሠረት በማድረግ አጠቃላይ ግንዛቤ እንዲኖርና በርዕሱ ላይ ውይይት ተጠናክሮ  እንዲቀጥል ማነሳሳት ነው::   

የጥናቱ ዓላማ

የዚህ ጥናት ዋና ዋና ዓላማዎች ቀጥለው የተዘረዘሩት ናቸው:: 
1.      እስካሁን ድረስ ስለብሄራዊ (ኢትዮጵያዊ) መግባባትና እርቅ  በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ምን እንደተጻፈ መመርመር  
2.     ብሄራዊ መግባባትና እርቅን በተመለከተ በሚገባ ያልተብራሩ ሃሳቦችን ለይቶ ማውጣት
3.     ብሄራዊ መግባባትና እርቅን በተመለከተ ወደፊት በጽንሰ ሃሳብና በተግባር ደረጃ ምን መደረግ እንዳለበት መጠቆም


የጥናቱ ዘዴና የመረጃ ምንጮች

በእርግጥ በድረ ገጾች በፌስቡክ በፓልቶክ ክፍሎች እንዲሁም በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ፕሮግራሞች ጉዳዩን (ብሄራዊ መግባባትና እርቅን) የተመለከቱ ውይይቶች ተካሂደው ይሆናል:: ለዚህ ጥናት እነዚህን ሁሉ የመረጃ ምንጮች ማካተቱ ጊዜ ወሳጅ መሆኑ ታምኖበታል:: በመሆኑም ከላይ የተዘረዘሩትን የጥናቱን ዓላማዎች ለማሳካት በዋና ዋና ድረ ገጾች የታተሙ መጣጥፎችን መመልከት ጠቃሚና ጊዜ ቆጣቢ ሆኖ ተገኝቷል:: አንድም የተቀናጀ ጽሁፍ በድረ ገጾች ማውጣት የተለመደ ነውና:: በመሆኑም ይህ ጥናት አራት ዋና ዋና ድረ ገጾችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅሟል:: እነሱም ECADF Ethiomedia Ethiopian Review እና Zehabesha ናቸው:: እነዚህ ድረ ገጾች በኢትዮጵያዊያን ዘንድ በደንብ የሚታወቁና ፖለቲካዊ ማኅበራው ባህላዊ ሃይማኖታዊ ምጣኔ ሃብታዊና ሌሎችንም ጉዳዮች ያካተቱ በርካታና ጠቃሚ ጽሁፎች የሚታተሙባቸው ናቸው:: በአጠቃላይ ሲታይ እነዚህ ድረ ገጾች ስለብሄራዊ መግባባትና እርቅ በቂ መጣጥፎችን እንደሚያትሙ ይገመታል::  

በተመረጡት አራት ድረ ገጾችም የተጻፈውን ሁሉ አንድ በአንድ መፈተሽ አሰልቺና ጊዜ ወሳጅ ከመሆኑም በላይ አላስፈላጊም ነው:: በመሆኑም የእያንዳንዱን ድረ ገጽ የመፈለጊያ ሳጥን Search box በመጠቀም በጉዳዩ ላይ የተጻፉትን መጣጥፎች በቀላሉ ማግኘት ይቻላል:: ቀጥለው የተዘረዘሩትን የአማርኛና የእንግሊዝኛ የመፈለጊያ ቃላት ወይም ቁልፎች keywords በመጠቀም አራቱም ድረ ገጾች ተፈትሸዋል::
·         National dialogue
·         National consensus
·         National reconciliation
·         ብሄራዊ ውይይት
·         ብሄራዊ መግባባት
·         ብሄራዊ እርቅ

በሌሎች ድረ ገጾች ጉዳዩን በተመለተ መጣጥፎች ታትመው ስለሚሆን Google በመጠቀም ተጨማሪ ፍለጋ ተካሂዷል:: ይህንም ለማድረግ ከላይ የተዘረዘሩትን የአማርኛና የእንግሊዝኛ  የመፈለጊያ ቃላትን ተጠቅሜአለሁ:: በአጠቃላይ ሲታይ አራቱ ድረ ገጾች በርካታ በብሄራዊ መግባባትና እርቅ ላይ የተጻፉትን ይዘው ተገኝተዋል:: ዳሩ ግን በፍለጋው ያልተገኙ ጥቂት መጣጥፎች ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል:: የጥናቱ ዋና ዓላማ ስንት እንደታተመ መቁጠር ሳይሆን ምን እንደተባለ መመርመር ስለሆነ ይህ ብዙም አያሳስብም:: ለአንባቢ ግልጽ መሆን ያለበት ሌላ ጉዳይ ቢኖር ይህ ጥናታዊ ጽሁፍ የሚያተኩረው የድኅረ 97 ምርጫ ጊዜን ነው:: ይህ ጥናት ምርጫውን ተከትሎ የነበሩትን የእርቅ ሙከራዎች አያጠቃልልም:: ምንም እንኳን ከዚህ ውጭ የጊዜ ገደብ ባይደረግም በርዕሱ ላይ የተጻፉት ጽሁፎች ለንባብ የበቁት ከ2010 ጀምሮ መሆኑን ግንዛቤ ወስጃለሁ:: የጥናቱ ዋና ዋና ግኝቶች ቀጥለው ቀርበዋል::      


የጥናቱ ግኝቶች

በአጠቃላይ ሲታይ ብሄራዊ መግባባትና እርቅን በተመለከተ 18 ጽሁፎች 2010 እስከ 2014 ታትመዋል:: ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ 2014 ብቻ የታተሙ ናቸው:: አብዛኞቹ (14) 2013 እና 2014 የተጻፉ ናቸው:: ሰባቱ በአማርኛ ሲጻፉ ቀሪዎቹ 11 ደግሞ በእንግሊዝኛ ተጽፈዋል:: 16 መጣጥፎች አርእስትና ሙሉ ይዘታቸው ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለቱ የተጻፉት ግን በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነው:: ቢሆንም ግን ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ከተነሱት አበይት ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳል:: አብዛኞቹ መጣጥፎችን ያቀረቡት ብዙውን ጊዜ በተለያዪ ሚዲያዎች የሚታወቁ ኢትዮጵያውያን ፕሮፈሰሮች ወይም ዶክተሮች ናቸው:: ሁሉም ጽሁፎች ከዚህ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ በጸሃፍት ስም በታተሙበት ዓመት በርዕሳቸውና ጽሁፎች በታተሙባቸው ድረ ገጾች ተዘርዝረው ይገኛሉ አንባቢያን ጸሃፍትን በቀላሉ ይለዩአቸው ወይም ያውቋቸው ዘንድ ሙሉ ስማቸውን በቅንፍ ውስጥ ጠቅሻለሁ:: አንድ ጽሁፍ በተለያዩ  ድረ ገጾች ታትሞ ቢገኝም ይህ ጥናታዊ ጽሁፍ ግን መጀመሪያ የተገኘበትን ድረ ገጽ ብቻ ይጠቅሳል::


ምንም እንኳን ሁሉም ጽሁፎች ብሄራዊ ውይይት መግባባትና እርቅ ዋና ጉዳያቸው ቢሆንም በዝርዝር ያተኮሩባቸው ጉዳዮች እንዲሁም የሰጧቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ግን የተለያዩ ናቸው:: በአጠቃላይ ሲታይ ግን የሚከተሉት ጉዳዮች በተለያዩ ጽሁፎች ተዳሰዋል:: 
·         የብሄራዊ እርቅ ጥቅምና አስፈላጊነት
·         እርቅ የሚያስፈልጋቸው አካላት
·         እርቁን ማን ማስተባበር ወይም መጀመር እንዳለበት
·         እርቁ እንዴት ሊካሄድ እንደሚችል 
·         ብሄራዊ እርቅና ፍትህ  እንዴት ሊታዩ እንደሚገባ


እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ የተገኙት 18 መጣጥፎች ምን እንዳስቀመጡ ቀጥሎ በአጭሩ ቀርቧል:: በቅንፍ የተመለከቱት የጸሃፍት ስምና መጣጥፎች የታተሙበት ዓመታት ናቸው:: ይህ ጽሁፍ የሚያተኩረው በዋናና ጠቅላላ ሃሳቦች ዙሪያ ስለሆነ ዝርዝር ጉዳዮችን ለመረዳት በአባሪ መልክ የተያያዙትን 18ቱን ጽሁፎች ማንበብ ይጠቅማል:: እንደገና የማሳስበው ጉዳይ ቢኖር 18ቱም ጽሁፎች ሁሉንም ከላይ የተዘረዘሩትን ንዑስ ጉዳች እንዳላተቱ ነው::    


የብሄራዊ እርቅ አስፈላጊነትና ጥቅም

ሁሉም ጽሁፎች ብሄራዊ መግባባትና እርቅ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ማኅበራዊ እሴቶችን ለመመስረትና ለማጽናት ወሳኝ እንደሆነ ያስገነዝባሉ:: እንዲሁም ከሌሎች የትግል ስልቶች አግባብነትና አተገባበር ጋር ብሄራዊ እርቅን ያወዳድራሉ ያነጻጽራሉ::  አብኞቹ ጽሁፎች ብሄራዊ እርቅ የሚያስፈልገው ኢትዮጵያ ያለችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ተባብሶ ወደ ከባድ ቀውስ እንዳትገባ ስለሚያደርግ እንደሆነ ያትታሉ:: ያሉትን ችግሮች በህዝባዊ አመጽም ሆነ በጦርነት ለመፍታት አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ተያይዞ ሊመጣ የሚችለው ቀውስ በቶሎ ማቆሚያ ሊኖረው እንደማይችል የብዙ አገሮችን ተሞክሮ በማንሳት ብዙዎች ያስጠነቅቃሉ:: ለምሳሌ ያህል ጥቂት ስለብሄራዊ እርቅ ጥቅም ወይም አስፈላጊነት የተሰጡት ማሳመኛዎች ቀጥለው ቀርበዋል::     
 • ውጥ በምርጫ ካልሆነ በጦርነት ካልተቻለ ህዝባዊ አመጽም አደጋ ካለው ብሄራዊ የእርቅ መንግስት ከመመስረት ውጭ ሌላ ምን አማራጭ የለም (መሳይ ከበደ 2013/2014)
 • የመንግስት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ  ስለሚፈልጉ ብሄራዊ እርቅን ለመተግበር የማይቻል አይደለም (ጋ 2013)
 • በቋንቋ በዘር በሃይማኖት በፖለቲካ ምክንያት ጥላቻ ያደረባቸውን አካላት ለማገናኘት ይረዳል (ዊት ተሾመ 2013)
 • ብሄራዊ እርቅ በሚገባ ከተያዘና ከተጠናቀቀ አምባገነኖችን ሳይቀር ነጻ የሚያወጣ ነው ሁሉም ተሳታፊ ስለሚሆን ጦርና የጦር ወሬዎች ታሪክ እየሆኑ ይሄዳሉ ይህ መንገድ የሰው ህይወትም ሆነ ንብረትና ሃብት አያጠፋም በመሆኑም ይህ የፖለቲካ መስመር ጭስ አልባ ሊባል ይችላል ስለሆነም በሚያስፈራ ዝምታ ውስጥ ያለውን የሰፊውን የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ ሊስብ ይችላል ለመግባባትና ለእርቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ስላለው አስፈላጊውን ድጋፍና ማበረታቻ  ማግኘት  አይከብድም በመጨረሻም ይህ የትግል ስልት ቀጣይነት ያለው ሰላምና እድገት እንዲመጣ ፈር ይቀዳል (ክሉ አባተ 2013/2014)
 • ቀጣይነት ላለው ሰላምና ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር መግባባትና እርቅ ማድረግ ወሳኝ ነው (ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቂ አኢጋን 2014  


የሚታረቀው ማን ነው?

ይህን ጉዳይ በተመለከተ በቂ ትንተና አልተሰጠበትም:: ጠቅለል ያሉና ግልጽነት የጎደላቸው ሃሳቦች ግን ተቀምጠዋል:: ከአብዛኞቹ ጽሁፎች ጀርባ ተቀምጠው የሚገኙት ነጥቦች እንደሚያመላክቱት ከሆነ እርቅ የሚደረገው ወይም መደረግ ያለበት በመንግስትና በህዝቡ መካከል ነው:: መንግስት በዳይና ህዝብ ተበዳይ ስለሆኑ የሁለቱ መወያየት መግባባትና መታረቅ ወሳኝ እንደሆነ ያብራራሉ:: እንዲሁም አንዱ ህዝብ ወይም ብሄር ከሌላው ጋር በጥርጣሬና በመፈራራት ስለሚኖር መታረቅ እንዳለበትም የሚጠቁሙ አሉ:: በተጨማሪም መግባባትና እርቅ በግለሰቦች መካከል ያለውን ያልጠራ ስሜትም ለማከም ማገልገል እንዳለበት የጠቆሙ አሉ (አኢጋን 2014):: ከዚህ ባለፈ ግን ጉዳዩን ብትንትን አድርጎ ያስቀመጠ ጽሁፍ የለም:: 

አንዳንዶች (ለምሳሌ ያዕቆብ ኃይለማርያም 2014) ማን ከማን ተጣላና ነው እርቅ የሚያስፈልገው ብሎ መቀለድ ዋጋ እንፍል ሲያስጠነቅቁ ሌሎች (ለምሳሌ ቴዎድሮስ ኪሮስ 2014; ተክሉ አባተ 2014 )ደግሞ በደፈናው በእርቁ መሳተፍ ያለባቸው ተቃዋሚ ኃይሎችና ድምጹን ያጠፋው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንዲሁም የፖለቲካ እስረኞች መሆን እንዳለባቸው ይጠቁማሉ:: አኢጋን ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ እርቅ የሚያስፈልገው በዘር በቋንቋ በሃይማኖትና በፖለቲካ በሚለያዩ ቡድኖች መካከል ሲሆን ከዚያ ቀጥሎ ብሄራዊ እርቅ መደረግ እንዳለበት ይጠቁማል:: በአጠቃላይ ሲታይ እርቅ የሚያስፈልገው በህዝብና በመንግስት መካከል ብቻ ሳይሆን ወረድ ብሎም በየደረጃው መከናወን እንዳለበት ጽሁፎች ጠቁመዋል:: ይሁን እንጅ መንግስትና ህዝብ ዋናዎቹ እርቅ የሚያስፈልጋቸው አካላት እንደሆኑ ሁሉም ጽሁፎች ያመላክታሉ::      


እርቁን ማን ያስተባብረው? 

ብሄዊ እርቁን ማን ማስተባበር እንደሚገባው ግልጽ የሆኑ ሦስት ዋና ዋና አማራጮች ተቀምጠዋል:: አንድ እርቁን መጀመርና ማስተባበር ያለበት መንግስት እንደሆነ ያተቱ አሉ (ለምሳሌ ዘላለም  እሸቴ 2014; መሳይ ከበደ 2013/2014 እና ገላውዲዎስ አርአያ 2010):: ፍላጎትና ዝግጁነት ካለው መንግስት ካለበት ብሄራዊ ኃላፊነትና ካለው አቅም አኳያ ይህን የማስተባበር ሥራ ቢወስድ እንደማይከብደው ይገመታል:: ሁለት እርቁን መምራት ያለባቸው  ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው የሚሉም አሉ (ለምሳሌ ዋለልኝ መኮንን 2012 ቴዎድሮስ ስ 2014):: ይህ አማራጭ ከፖለቲካው ሜዳ በመንግስት እየተገፉ ያሉት ኃይሎች ሂደቱን እንዲመሩት ያመቻቻል:: ሦስት መንግስትና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና የእርቁ አካል ስለሆኑና በዳይና ተበዳይም ስለሆኑ ነጻና ገለልተኛ ኢትዮጵያውያንን ያቀፈ አስታራቂ ግብረ ኃይል የእርቁን ሂደት መምራት አለበት የሚሉም አሉ (ለምሳሌ ተክሉ አባተ 2013 2014)::

ከነዚህ አማራጮች ለየት ያሉም አሉ:: ሁሉን አቀፍ የምክክር ጉባዔ እንዲጠራ ያሳሰቡም አሉ (ሰሎሞን ታረከኝ 2011):: መገናኛ ብዙኅን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚችሉ ቢጠቀስም ሂደቱን ማን እንደሚመራውና እንደሚጀምረው ግን ግልጽ አይደለም:: እንዲሁም ጣቱ ትውልድ ወደብሄራዊ እርቅ የሚያደርሰውን ውይይትና ምክክር በበላይነትና በባለቤትነት መምራት እንዳለበት ያሳሰቡ አሉ (አለማዬሁ ማርያም 2012):: የተማረጣቱ ትውልድ የትናንቱ ትውልድ ከሚዳክርበት የግራና የቀኝ የፖለቲካ አመለካከት ነጻ ሆኖ የእርቁን ሂደት ቢመራው እጅግ እንደሚሻል ተጠቁሟል:: ይህ እንዴት መካሄድ እንዳለበትም የመነሻ ሃሳቦች ተሰጥተዋል::    


እርቅ እንዴት ይካሄድ?

ብሄዊ መግባብትና እርቅ እንዴት መካሄድ እንዳለበት በርከት ያሉ ትንተናዎች ተሰጥተዋል:: ብዙዎች (ለምሳሌ ተክሉ አባተ 2014; ዘላለም እሸቴ 2014; ሰሎሞን ታረከኝ 2011; አለማዬሁ ገብረ ማርያም 2012; ላውዲዎስ አርአያ 2010)  ከእርቅ በፊት ቀጣይነት ያላቸውና ሁሉን አቀፍ ክርክሮችና ውይይቶች መካሄድ እንዳለባቸው ጠቁመዋል:: ብሄራዊ ክርክሮችና ውይይቶች መንግስትና ተቃዎሚ ድርጅቶች በእኩልነት ተናግዱ: የእያንዳንዳቸውን ጠንካራና ደካማ ጎን መለየት የሚያስችሉ: እንዲሁም በእውነት ላይ የተመረኮዙ መሆን እንዳለባቸው ተጠቁሟል:: ሌሎች ስለእርቅ ሂደት የተዘረዘሩ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው::
 • በውይይቶች ጊዜ እውነታን መለየትና እውቅና መስጠት (ያዬ አበበ 2014)
 • ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ መለየት: ከዚያም የስምምነት ሰነድ መፈራረም (ገለታው ዘለቀ 2014)
 • ችግሮችን መመርመር: ተጎጅዎችን መለየት (ዳዊት ተሾመ 2013)
 • የተሰሩ ወንጀሎችን መለየት: መከላከያና ደህንነት ተቋማት ገለልተኛ ድረግ: በነጻ የመናገር መብት ማስከ (ዋለልኝ መኮንን 2012)
 • መጀመሪያ ወጣቶች ኢ-መደበኛ ውይይቶችን በአካባቢያቸው መጀመር: ንቃተ ኅሊናን የሚያዳብሩ መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀ: ውይይቶች ግልጽነትን ዲሞክራሲያዊ አሠራርን የተከተሉ: ሰብአዊ መብቶችንና ነጻነትን ማዕከል ያደረጉ ይሁኑ:: የራስን ችሎታና አቅም መመዘን: ያሉትን ተቋማት ለዚሁ ዓላማ መጠቀም: ከትናንቱ ትውልድ የአዙሪት ፖለቲካ መጠንቀቅና ከስህተቱ መማር (አለማዬሁ ገብረ ማርያም 2013)
 • መንግስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገር እድገት አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ ይመን:: እነሱንም ከማሳደድና ከመፍራት ይልቅ ያቅርባቸው:: በዘር ላይ የተመሰረተውን የፌደራል አወቃቀር እንደገና ያጢነው (ገላውዲወስ አርአያ 2010)
 • የታሰሩትን ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲና የሃይማኖት መሪዎችና አባላትን በሙሉ መፍታት፤  የጸረ-ሽብርተኛ አዋጅ መሰረዝ፤ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕዝባዊ ድርጅቶች አባላትና መሪዎችን በሽብርተኛነት የተፈረጁትንም አጠቃሎ የያዘ አንድ ጉባዔ በአዲስ አበባ ማካሄድ (ዕቆብ ኃይለ ማርያም 2014)
 • የብሄራዊ እርቅ መድረኮች ይዘጋጁ (ቴዎድሮስ ኪሮስ 2014)
 • ልብ የሆነ ይቅርታ መጠየቅና ማድረግ (ን 2014) 

እርቅና ፍትህ  

ብሄራዊ መግባባትና እርቅ በሚጀመርበት ጊዜ የፍትህ አገሯ ወዴት ይሆናል? ይህ ጥያቄ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ በቂ መልስ ያገኘ አይመስልም:: ከ18ቱ መጣጥፎች ውስጥ ሦስት የሚሆኑት ብቻ ይህን ጉዳይ በግልጽ አንስተዋል:: በጣም  ለተበደሉ ወገኖች ፍትህ (ለምሳሌ ካሳ) መደረግ እንዳለበት ጠቆም ያደረጉ አሉ (ያዬህ አበበ 2014; ን 2014):: በጣም የተበደሉት ወገኖች እነማን እንደሆኑና ምን አይነት ካሳ በማን መሰጠት እንዳለበት ግን የተብራራ ነገር የለም:: ከሁሉም ጽሁፎች ገለታው ዘለቀ (2014 ገጽ 4)የጻፉት የእርቅና የፍትህ ግንኙነት እጅግ በተሻለ መልኩ እንደሚከተለው ያብራራል:: ዋናው መልእክት እርቅ በሚደረግበት ጊዜ እንደአስፈላጊነቱ ፍትህም ሥራ ላይ ሊውልበት የሚችል እድል እንዳለ ያመላክታል:: የእርቅና የፍትህ ውሳኔዎች በአንድ ላይ ተጣጥመው መሄድ እንደሚችሉ ባህላችንን በምሳሌነት እያነሳ ይተነትናል::   

በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ብሄራዊ እርቅን በኢትዮጵያ የሚያየው እንደዚህ ነው። በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ብሄራዊ እርቁ ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስን መሰረት ያደረገና በሚያድግ ዴሞክራሲ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ስምምነት ማለት ነው። ይህ ማለት ግን ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ቦታ የለውም ማለት ኣይደለም። በኣሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ሙስናና ከፍተኛ ወንጀል እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች ይህንን ኣሳባችንን እያዩ እንደ ጅልነት ኣይተው ከስልጣን እስኪወርዱ በግፋቸው እንዲቀጥሉ በር ኣይከፍትም። የብሄራዊ እርቅ ሰነዱ እንደነዚህ ኣይነት ሰዎችን በቡድን እያየ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ወደ ፍርድ ሊያመጣቸው መቻሉ ኣያጠያይቅም። እንደ ቡድን እንደ ሃገር ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን ዝግ እያለ ሊሰራጭ በሚችል የሪዲስትሪቢዩሽን ዘዴ ተመጣጣኝ እድገት ለማምጣት መስማማት፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎን ከባህላዊ ውህደት ስምምነት ኣንጻር ኣይቶ ከብሄር ፖለቲካ ኣውጥቶ በኣንድ ብሄራዊ ማንነት ስር ለመገንባት መስማማት፣ ዋና የሃገሪቱን ቋንቋዎችን ቁጥር መጨመር ኣጠቃላይ ፈውስን ለማምጣት ይጠቅማል። ኢትዮጵያ ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ላይ እንድታተኩር የሚያደርጋት ለዘላቂ ሰላምና ልማት ኣንድነት የሚረዳት ሲሆን ይህ የፍትህ ኣሰጣጥ ዘዴ በኢትዮጵያ ቡድኖች ዘንድ የተባረከና የሚበረታታ ነው። የኦሮሞ ስርዓትን ብናይ ለሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ትልቅ ቦታ ኣለው። ይቅር ማለትን፣ በዳዩን ከመቅጣት ይልቅ ተበዳዩን መካስን ያበረታታል። ኣማራው ኣካባቢ ያለውን የሽምግልና ስርዓት ስናይ በኣብዛኛው ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ የሚበረታታበት ሁኔታ ኣለ። በደቡብ፣ በምስራቅ በተለይም በሶማሌ ክልል ይህ የፍትህ ስርዓት ከፍተኛ ተጽእኖ ኣለው ገለታው  


የማጠቃለያ ሃሳቦች

ይህ ጥናት ብሄራዊ መግባባትና እርቅን በተመለከተ በርካታ ጠቅለል ያሉ ጉዳዮችን ዳሷል:: ዝርዝር ትንተናዎችን ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት መጣጥፎች ማግኘት ይቻላል:: ለማጠቃለል ያህል ግን ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት ያስፈልጋል::

አንደኛ ምንም እንኳን የተዳሰሱት 18ቱ መጣጥፎች የብሄራዊ መግባባትና እርቅን ጠቀሜታና አስፈላጊነት ከሌሎች የትግል ስልቶች ጋር በማነጻጸርና በማወዳደር ለማቅረብ መሞከራቸው ክፉ ባይሆንም ጉዳዩን በሌላ መነጽር መመልከቱ ይበልጥ ጠቃሚ ነው:: ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ተጀምሮ የተወሰነ አጓጊ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ሌሎችን ትግሎች ማቆም ላያስፈልግ ይችላል:: ሌሎች ትግሎች (ለምሳሌ የተቀናጀና ደረጃ በደረጃ የሚመራ ህዝባዊ እምቢተኝነት http://tekluabate.blogspot.no/2014/08/blog-post_6.html#more) ምናልባትም መንግስት የእርቁን ጉዳይ በሚገባ እንዲያጤነው ሊያስገድዱት ይችላሉ:: በመሆኑም የእርቅን ጠቀሜታ ለማውሳት ሌሎች ትግሎችን ማኮሰስ የግድ አይጠበቅም::

ሁለተኛ የተወሰኑ ጽሁፎች ህዝብ ለህዝብ መታረቅ እንዳለበት አሳስበዋል:: ምንም እንኳን ሃሳቡ በራሱ ክፉ ባይሆንም ለበርካታ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ የሆነውን አካል ማለትም መንግስትን ላላ አርገን እንድንይዝ የሚጋብዝ :: በመጀመሪያ ደረጃ ህዝብ ለህዝብ ሊጣላ አይችልም:: ከበስተጀርባ ያሉ ተንኳ የመንግስት ፖሊሲዎችና ፕሮፓጋንዳዎች የህዝብን ልብ ይከፍላሉ:: መንግስት ከትንኮሳው ሁሉ ታቅቦ ህዝቦች በሰላምና በአንድነት እንዲኖሩ ቢሰራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የነበረን መከባበርና መተሳሰብ ይመለሳል:: ስለዚህ መታረቅ ያለበት መንግስ ከህዝብ ጋር ነው ብዬ አምናለሁ::

ሦስተኛ መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እውነተኛ እርቅን ጀምረው ማስተባበር ይችላሉ ማለት ዘበት ነው:: መንግስት እንደግለሰብ ቂመኛ በቀለኛና ትምክህተኛም ነው:: ለተቃዋሚዎች ያለው ንቀትና ጥርጣሬ መጠን የለውም:: እርቅን እሱ ቢጀምር የመሸነፍና የመዋረድ ያህል ይመለከተዋል:: ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ከመንግስት ጋር ያላቸው ቅራኔ እርቅ ለመጠየቅ የሚያበቃ አይመስልም:: ሰጥቶ የመቀበልና የማሳመን ችሎታና ፍላጎት እስካሁን አላየንም:: በመሆኑም ሌላ ገለልተኛና አንጻራዊ በሆነ መልኩ ንጹህ ኢትዮጵያውያን የተሰባሰቡበት አካል ያስፈልጋል:: ይህን አካል የሚያቋቁመው አካል: የሚቋቋምበት መስፈርት: የሚኖረው ዝርዝር የሥራ ድርሻ: የሚጠቀማቸው ዘዴዎች: ወዘተ ግን ጥርት ብለው ለውይይት ቢቀርቡ የተመረጠ ነው እላለሁ:: እንዲሁም ፍትህና እርቅ ምን ያህል የሚዛመዱና የሚቃረኑ እንደሆነ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት አስቀድሞ መተንተን ያስፈልጋል::

በአጠቃላይ ይህ አስተባባሪ ኃይል ከእርቅ በፊት በእርቅ ጊዜና ከእርቅ በኋላ ሊሟሉ የሚገባቸውን ሁኔታዎች እጅግ በዝርዝር አዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አቅርቦና በውይይት አዳብሮ ሊንቀሳቀስ ይገባል:: ይህ ቀላል ሥራ ስላልሆነ የሚመረጡት ሰዎች ስሜታቸውን የሚቆጣጠሩና የሞራል ብስለት ያላቸው: አዋቂዎችና አስተዋዮች: እንዲሁም የመግባባትና ጫናን የመቋቋም አቅም ያላቸው ሊሆን ይገባል:: ልዩ ልዩ አይነት መስዋዕትም ለመክፈል የተዘጋጁ መሆን አለባቸው:: በመሆኑም ብሄራዊ መግባባትና እርቅ በብርቱ ልፋትና መከራ የሚመጣ እንጅ እንደሚታሰበው ሰላማዊ ብቻ ላይሆን ይችላል::    

የመጀመሪያው ችግር የሚሆነው ይህን አስታራቂ ኃይል ማቋቋም ነው:: ማን ነው ይህን ሊያነሳሳው የሚችለው? በተለያዩ  አካላትስ ተቀባይነት ይኖረዋል? ፍላጎትና ለኢትዮጵያ መልካም ራእይ ያለው ማንኛውም አካል ሊጀምረው ይችላል:: ቢያንስ ቢያንስ ይህ ጥናታዊ ጽሁፍ የገመገማቸውን 18ቱን በብሄራዊ መግባባትና እርቅ ላይ ያተኮሩ መጣጥፎችን ያቀረቡት ምሁራን በመመካከር ለጉዳዩ የሚሆን መሪ ሃሳብ roadmap ማዘጋጀትና ለውይይት ማቅረብ ይችላሉ:: ጥናቱን በማካሂድበት ጊዜ የታዘብኩትና ወደፊት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ግን አለ:: ሁሉም መጣጥፎች ራሳቸውን የቻሉና ሌላውን ለድጋፍም ይሁን ለትችት በፍጹም የማይጠቅሱ ናቸው:: ስለአንድ ጉዳይ በሚጽፉ ሰዎች መካከል ምንም አይነት መናበብ እንደሌለ አመላካች ነው:: ሁሉም የግል ሩጫውን ተያይዞታል:: ይህን አቁመን በአንድ ጉዳይ ላይ የምንጽፍ ሰዎች መናበብ ብንጀምርና የመነሻ ሃሳብ ብናቀርብ ብሄራዊ ግዴታችንን እንደመወጣት ይቆጠራል:: የያዘውን የወረወረ ፈሪ አይባልም!!!

ስለብሄራዊ እርቅ የተጻፉ ጽሁፎች

በአማርኛ የተጻፉ

በእንግሊዝኛ የተጻፉ


ነጻነት ለኢትዮጵያ!!!
ገንቢ አስተያየት ወይም ጥያቄ ካለዎት በteklu.abate@gmail.com ይላኩ!

ተልዕኳችን | Our Mission

“65 ፐርሰንት” ትርጉም? የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ተልዕኳችን ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው። ግባችን ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

What is “65 percent”? 65% of Ethiopia’s population is under 24 years old. Our mission is to model a culture of political concensus for the 65%. Our goal is to advocate for, and initiate reconciliation and consensus among Ethiopians.

Post Archive