Dec 14, 2015

ፎረም 65፦ ድርቅ እና የተማሪዎች ተቃውሞ የአለመግባባት አደጋ መገለጫዎች ናቸው

03/04/2008 ዓ.ም.

አለመግባባት ለአገራችን ህልውና የሚፈጥራቸው አደጋዎች በየጊዜው እየጨመሩና እየተስፋፉ መምጣቱ በእጅጉ አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል። መንግስት ዋና ዋና ችግሮች ላይ አገራዊ መፍትሄን ለማግኘት ከህዝብ፣ ከህጋዊ ተቃዋሚዎችና ከዲያስፓራው ማህበረሰብ ጋር መግባባት ላይ ካልደረሰ አለመግባባት ወደ ቀውስና ግጭት ማደጉ አሳሳቢ ነው።

መንግስት ለድርቅ አደጋ የተዳረጉ አስራ አመስት ሚሊዮን ዜጎችን አስፈላጊውን እርዳታና ድጋፍ እንዲያገኙ ሁሉንም ያሳተፈ፡ ግልጽና አፋጣኝ መፍትሄ ካልፈጠረ፤ እንዲሁም የኦሮሚያ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ላይ የሚያሰሙትን ተቃውሞ በማግባባት መፍትሄ ከመፍጠር ይልቅ ተማሪዎችን በመግደልና በማሰር ብቻ አላማውን የማስፈጸም አሰራሩ ከቀጠለ ለአገራችን ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አደጋ ነው።

የድርቅ አደጋ

በድርቅና ረሃብ በተደጋጋሚ ሚጋለጡ አገሮች ሚገኙበትን ሁኔታ ለመለካት የተባበሩት መንግስታት የሚጠቀመበት ባለ አምስት ደረጃ መስፈርት ነው። በ1ኛ መስፈርት ላይ ርሃብም ሆነ ድርቅ አደጋ የሌለባቸው አካባቢዎች ይገኛሉ። በ2ኛ መስፈርት የድርቅና ርሃብ ውጥረት ውስጥ ያሉትን ያመለክታል። በ3ኛ ደረጃ በድርቅና በርሃብ ቀውስ ደረጃ ላይ የደረሱት ይገኛሉ። በ4ኛው መለኪያ ውስጥ ሚገኙት ህይወታቸው በርሃብ አደጋ ላይ የወደቁ ናቸው።

5ኛው ደረጃ አስከፊውና ብዙዎች በርሃብ የሚሞቱበት ደረጃ ነው። በኢትዮጵያ ዛሬ 4ኛ ደረጃ ውስጥ የገቡ አካባቢዎች መኖራቸውን ዘገባዎች ይጠቁማሉ (ካርታውን በሃሳብ መስጫ ላይ ይመልከቱ )። በተጨማሪም በዘገባዎቹ መሰረት አፋጣኝ እርዳታ ካልተደረገ በ3ኛ ደረጃ ላይ ያሉ ብዙዎች ወደ 4ኛ ደረጃ መግባታቸው እይቀርም። (የካርታ ምንጭ IRIN*)
በአገራችን የዘውድና የወታደራዊው መንግስታት እንዲናጉና እንዲሁም እንዲወድቁ ድርቅ ምክንያትና ሰበብ ነበር። አገራችን ዛሬም በፖለቲካ፥ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ውጥረቶችና ቅራኔዎች ውስጥ በመገኘቷ፥ ዛሬ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በአፋጣኝ መልስ ካላገኘ፥ ውጥረቶቹና ቅራኔዎቹ የፈጠሯቸው ስንጥቆች በድርቁ ምክንያት ሰፍተውና የድርቁ መዘዝ ለፖለቲካ ፍጆታ ውሎ ስንጥቆቹ ወደ አስከፊ ሁኔታ ሊዳርጉን እንደሚችሉ እንሰጋለን።

15 ሚሊዮን ህዝብን ለ4ኛ ደረጃ የርሃብ አደጋ ሊዳርግ ሚችለውን ድርቅ ገዢውም ሆነ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ከማዋል ባለፈና ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ በጥንቃቄና በቅልጥፍና ከአገር ውስጥ፣ ከዲያስፖናራና ከአለማቀፋዊው ማህበረሰብ እርዳታ ማሰባሰብ ላይ በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ እናቀርባለን።

የተማሪዎች ተቃዉሞ

የኦሮሚያ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ እቅድ ላይ ተቃውሞ ባሰሙበት በ2006 ዓ.ም. ፓሊስ የወሰደው የሃይል እርምጃ ካደረሰው ግድያ፡ እስራትና እንግልት ያልተማረውና ያልተጸጸተው መንግስት፡ እንደገና ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተደረጉት ተቃዉሞዎች ላይም እየወሰደ ያለውን የሃይል እርምጃ አጥብቀን እናወግዛለን።

ወጣቶች በአገራቸው ሃሳባቸውን የሚገልጹበትን የፓለቲካ ምህዳር በማዘጋጀት፣ በወይይትና በመተማመን መግባባት ላይ መድረስ እየተቻለ፡ መንግስት የደም ማፍሰስ መንገድ መምረጡ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ቁማር እንደ መጫወት ነው።
ቁማር ማለት በአቋራጭ ያለሂደት፣ ያለፅናትና ያለታታሪነት ውጤታማ የመሆን ስሌት ነው። መንግስት የሚያወጣቸውን ፓሊሲዎችና ዕቅዶች ያለ ህዝብ ግብአት እንዲፈፀሙ በሚያደርገው የጉልበተኝነት ባህሪው በአገሪቱ፥ በህዝቦችና በራሱም ህልውና ላይ ቁማር እየተጫወተ ነው።

አገሪቱ የምትገኝበት የድርቅ አደጋ፥ የኑሮ ውድነት፥ የፓለቲካ ምህዳር መጥፋትና የአንድ ፓርቲ ስርዓት መስረፅ የሚያመላክቱት አመራሩ የሚወስደው ስሌት በእጅጉ ቁማራዊ መሆኑን፣ ካለፉት ስርዓቶች ዋና ስህተቶች አለመማሩንና በተለይም ህዝብን የመናቅ፣ ያለማዳመጥ፣ ከፓርቲው መስመር ውጪ የሌላው ዕይታም ሆነ ርዕዮት ለአገሪቱ ምንም ፋይዳ የሌለው አድርጎ የማየት ዕብሪት ናቸው።

የህዝብን ብሶትና መከራ አዳምጦ በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት ያልቻለው ንጉሳዊው ስርዓትም ሆነ፥ ከጉልበት ውጪ መፍትሄ መፀነስ ያልቻለው ወታደራዊው መንግስት ዛሬ የሉም። ኢሕአዴግ ቁማራዊ አኪያሄዱን አቁሞ የራሱን ህልውናና ጥቅም በዘለቄታዊነት ሊያስጠብቅለት ሚችለውን የመግባባትን መንገድ እንዲመርጥ ጥሪ እናቀርባለን።

ማጠቃለያ


መንግስት የአገሪቱን የፖለቲካ ቅራኔ ለማርገብ፦

(1ኛ.) ሚጠበቅበትን ሰፊ ሚና እንዲጫወት፣

(2ኛ.) በብሔራዊ እርቅና መግባባት አገሪቱን ወደ ተረጋጋ የፖለቲካ ምዕራፍ ውስጥ እንድትገባ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያካተተ የመግባባት ሂደት ላይ በፋናወጊነት እንዲሳተፍና፣

(3ኛ.) አገራዊ አደጋዎችን በጋራና በፍጥነት እንድንወጣ ፖለቲካዊ እንቅፋቶችን እንዲያነሳ እንጠይቃለን።
የድርቅን አደጋ በሚመለከት ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች ድርቁን ለፖለቲካ ፍጆታ ከማዋል ይልቅ ቅድሚያ በርሃብ የተጋለጡትን ወገኖች መርዳት ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ እናቀርባለን። መንግስት በድርቅ አደጋ ለተጋለጡ ዜጎች እርዳታ በአፋጣኝ ለማሰባሰብ የሚያስችል፣ ፓለቲካዊ ያልሆነ፣ ገለልተኛ ጊዜያዊ አገራዊ ግብረሃይል አቋቁሞ መፍትሄ ላይ እንዲያተኩር አጥብቀን እናሳስባለን። ይህ ካልሆነ ግን የኢሕአዴግ መንግስት፡ እንደ ቀድሞ መንግስታት ሁሉ፡ በርሃብ ሰለባ ለሚሆኑና ለሆኑ ዜጎች ተጠያቂ ነው።

በዚህ አጋጣሚ ለተገደሉ ተማሪዎች ቤተሰቦች ሃዘናችንን እንገልጻለን።

ፍትህ ለተገደሉ የኦሮሚያ ተማሪዎች!

መግባባትን እናውርስ! 

ፎረም 65**

* http://newirin.irinnews.org/…/how-bad-is-the-drought-in-eth…, Accessed on Dec 7, 2015
** "ፎረም 65" በብሔራዊ እርቅና መግባባት ላይ ሳምንታዊ ዝግ ውይይት የሚያደርግ የ65Percent.org መድረክ ነው።

-----
ስለ 65Percent.org

የ65% ትርጉም፦ የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው።
ግባችን፦ ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።
ተልእኳችን፦ ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው።

ተልዕኳችን | Our Mission

“65 ፐርሰንት” ትርጉም? የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ተልዕኳችን ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው። ግባችን ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

What is “65 percent”? 65% of Ethiopia’s population is under 24 years old. Our mission is to model a culture of political concensus for the 65%. Our goal is to advocate for, and initiate reconciliation and consensus among Ethiopians.

Post Archive