Aug 6, 2014

ብሔራዊ መግባባት ወይስ አገራዊ ውድመት? በያዕቆብ ኃይለማርያም ዶ/ር

ያዕቆብ ኃይለማርያም ዶ/ር
አንዳንድ እንደዘረኝነት፣ ጐሰኝነትና የሃይማኖት ጥላቻ ስለመሳሰሉ አጸያፊ ክስተቶችና ሕዝባዊ ግንኙነቶች ማንሳትና ስለእነርሱም መጻፍ የሚቀፍ ከመሆኑም በላይ፤ ያልሆነ ስም ሊያሰጥና በዘረኝነት ተጠቃሚ የሆኑ አካላትንም ሊያስከፋ ይችላል፡፡ ሆኖም ሳይመሽ አገርን ከውድቀት ለመታደግ እና ሕዝብን ከጥፋት አፋፍ ለመመለስ ሲባል፤ ከአገርና ከሕዝብ የሚበልጥ የለምና ይሉኝታን ዋጥ አድርጐ በፍርሃት ሳይገደቡ፣ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ሳይሽሞነሞኑ እነዚህን አገር በታኝ ክስተቶችን በአደባባይ አፍርጦ ለማውጣት ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ሰው መሆንም በቂ ነው፡፡

ጥላቻና ገደብ የለሽ የአገር ሀብት ዝርፊያ በተለይም የዘር ጥላቻና ዘረኝነት በሩዋንዳ ያስከተለውን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ዘግናኝ እልቂትና ጭካኔን ያየና፤ የእነዚያ አክራሪ የሁቱ ጐሣ አባላትና መሪዎቻቸውን ሰይጣናዊ ድርጊቶች በፍርድ ቤት ከስሶ ሁኔታውን በዝርዝርና በጥልቀት የተረዳ ኢትዮጵያዊ፤ የዘርና የጐሣ ጥላቻ ያስከተለውን እልቂትና የአገር ውድመት በአገሩ ላይ እንዳይከሰት፣ ምንም ቢያስከፍልም ሆነ ምናልባትም የቁራ ጩኸት ቢሆን እንኳን ‹‹ውርድ ከራሴ›› በማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊረዳው በሚችልበት ቋንቋ በግልጽ የማስረዳት ኃላፊነት አለበት፡፡ በሩዋንዳ ከሰላሳ ዓመታት በላይ ሲያመረቅዝ የቀዬው የዘር ጥላቻ ወደ እልቂት ሊያመራ እንደሚችል ገና ከጠዋቱ ያስጠነቀቁ ምሁራን ከፋፋይ ሽብር ነዢዎች ተብለው እንደተፈረጁ ሁሉ፤ አሁንም ይህ ማስጠንቀቂያ ተመሳሳይ ዘለፋ ያስከትል ይሆናል፡፡ ዋናው ነገር ግን በአገራችን ላይ እያንዣበበ ያለውን አደጋ ሕዝብና መንግሥት ይረዱት እንጂ፣ ሌላው ሁሉ ገብስ ነው፡፡

የዘር ጥላቻንና የጐሣ ግጭቶችን በጠቅላላው ጐሰኛነትንና ጐጠኛነትን፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ገና ድሮ ልናልፋቸው በተገባ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እኮ፣ ከብዙ አገራት ቀድማ አገራዊ አንድነትና ሉዐላዊነት የተጐናጸፈች፣ ጥልቅ ታሪክና የራስዋ ፊደልና የዳበረ ባህል ያላት አገር ነች፡፡ ሕዝቡም ለብዙ ምዕተ ዓመታት ክፉውንና ደጉን እየተጋራ በነፃነት የኖረ ሲሆን፤ ትናንት የተፈጠሩ አገራት ዘረኝነትንና ጐጠኝነትን አልፈው ሄደው አገራዊ አንድነት ሲፈጥሩ፣ እኛ በብሔረሰቦች መብት ስም እንዴት በዘረኝነት ውስጥ እንደነጋገራለን? ኢሕአዴግ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ በመታወቂያ ካርድ እየለየ በጐሣ ወይንም በብሔር ከረጢት ውስጥ እንዲገባ ከመደንገጉ በፊት፣ ይህንን ዛሬ የተንሰራፋውን ጐሰኝነት ልናልፈው ተቃርበን ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በሩዋንዳ የተካሄደውን ጭፍጨፋ ቀላል ካደረጉት ነገሮች አንዱ፣ ሕዝቡ በነቂስ ዘሩን ወይንም ብሔሩን የሚያመላክት መታወቂያ አውጥቶ እንዲይዝ መደረጉ ነበር፡፡

በኢትዮጵያም ይህ አላስፈላጊ የሆነ ዝርዝር ሁኔታ፣ ማለትም ብሔረሰብ በመታወቂያ ካርድ ላይ እንዲጠቀስ የመደረጉ ጥቅም ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ጐሰኝነትንና ጐጠኝነትን ልናልፋቸው ተቃርበን እንደነበረ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ከሰላሳ ዓመታት በፊት ዩኒቨርስቲ አካባቢ፣ አንድ ሰው ከኢትዮጵያዊነቱ ውጭ አማራ ይሁን ኦሮሞ፤ ጉራጌ ይሁን ከምባታ አይታወቅም ነበር፡፡ ቢታወቅም በጓደኛ አመራረጥ ላይ የብሔር ማንነት ምንም ተጽእኖ እንዳልነበረው በዩኒቨርስቲው ያለፉ ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ በጊዜው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ኢዲዩ፣ ኢሠፓ፣ ወዘተ ሕብረ ብሔራዊ ድርጅቶች ሲሆኑ፤ ከሕወሓትና ከኦነግ ውጭ ጐሰኝነትን መሰረት ያደረገ ፓርቲ አልነበረም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊቀበሉት የሚገባ አንድ ሐቅ ግን አለ፡፡ 

ይኸውም ዛሬ የአንድ ጐሳ ወይንም ብሔር አባል ቋንቋውን የመናገርና የማበልጸግ፣ በባህሉ መኩራትና መተግበር፣ የውስጥ አስተዳደሩን ራሱ የመምራት መብት እንዳለው አጠያያቂ ያለመሆኑ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግጋት እውቅና ያገኘ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም እንዲህ ዓይነት ያልተገደበ መብት መገንጠልን እንደማይጨምር አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የተረዱት አይመስልም፡፡ የመገንጠል መብት መቼና በምን ሁኔታ ይፈቀዳል የሚለው ጥያቄ ሰፊ ርዕስ በመሆኑ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡ የእነዚህ የብሔረሰብ መብቶች መከበር፣ ዘረኝነትን አጥፍተው ብሔራዊ አንድነትን ያዳብራሉ እንጂ አያዳክሙም፡፡
ወደ ዋናው ጉዳያችን እንግባ፡፡ በስውር ቋንቋ ሳንሸፋፍነው፣ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ሳናሽሞነሙነው ከተነጋገርን፤ በአገራችን የዘር ጥላቻ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እየተንሰራፋና እየተስፋፋ መሄዱ፣ ሰው ሁሉ ያወቀው ጸሐይ የሞቀው እውነታ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በእነዚህ 23 ዓመታት ውስጥ የዘረኝነት ክስተቶች የተገለጡባቸው ቦታዎችና ሁኔታዎች በጣም ብዙ ስለሆኑ፣ ለናሙና ያህል ጥቂቶችን ብቻ እንጥቀስ፡፡

በብሔር ወይንም በዘር ልዩነት ምክንያት ከሕይወት መጥፋት ጀምሮ ያሉ ግጭቶች ያልተከሰቱባቸው የአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ጥቂቶች ናቸው፡፡ አንድ ጐሳ ወይንም ብሔር ከሌላ ጐሳ ጋር ተጋጭቶ፤ ይህን ያህል ሰው ሞተ፣ ይህን ያህል ንብረት ወደመ የሚል ዜና ሰርክ እየሰማን ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት አንዳንድ ሃፍረተ ቢስ ኃላፊነት የጐደላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በፌስ ቡክ አማካይነት የሩዋንዳ እልቂት በኢትዮጵያ መደገም አለበት የሚል አስደንጋጭ መልእክቶች እንደሚያስተላልፉ ሳንረዳ አንቀርም፡፡ ጨቅላ ሕፃን ይዛ የእለት ጉርስዋን የምትለምነው የእኔ ቢጤ እንኳን፣ ብሔሯን ከምትለምነው ሰው መደበቅ አለባት፡፡ አለበለዚያ ተለማኙ ሰውዬ የማይወደው ብሔር አባል መሆኗን ካወቀ፣ የዳቦ ሳንቲም መንፈግ ብቻም ሳይሆን ብሔሯን እየጠቀሰ ሊቀልድባት ይችላል፡፡

መንግሥት አለ ወይ እስኪባል ድረስ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን፣ የክልሉ ብሔር አባላት አይደላችሁምና ከክልሉ ወይንም ከወረዳው በዚህ ቀናት ውጡ እየተባለ፤ የአካባቢው ሕዝብ ማፈናቀሉን ቢቃወምም እንኳን፣ ባለስልጣናቱ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ሜዳ እንዲወድቁ አድርገዋቸዋል፡፡ በጊዜው በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቁጣ በታጀበ ንግግራቸው፣ በቤኒሻንጉል አማርኛና ኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ከኖሩበት ክልል ማፈናቀል ሕገ-ወጥ መሆኑን እና ጥብቅ እርምጃም በአስቸኳይ እንደሚወሰድ ገልጸው ነበር፡፡ 

አስገራሚው ነገር ደግሞ ተፈናቃዮቹ ወደ ቤት ንብረታቸው ካለመመለሳቸውና መንግስት ነገሩን ናቅ አድርጐ ከመተው ባሻገር፣ እንዲያውም ተጨማሪ ዜጐች እንዲፈናቀሉ ተደርጓል፡፡ ‹‹አለማወቅ ደጉ›› ሆነና ነው እንጂ፤ በዓለም አቀፍ ወንጀለኝነት የሚታወቀው የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈጽሙና የፈጸሙ ባለስልጣናት ምን እንደሚጠብቃቸው ቢያውቁ እንቅልፍ በዓይናቸው ባልዞረ ነበር፡፡ ከሰባ አመታት በፊት ለፈጸሟቸው ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የቀድሞ ናዚ ጀርመናውያን፤ ስፔን ውስጥ ተይዘው፣ በዚሁ በያዝነው ዓመት ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ የቀድሞው ዩጐዝላቪያ መሪ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ፊት የቆመው፣ ግድያ ቢኖርም ግን በዋናነት ሰርቦች ሙስሊሞችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅለው ካምፕ ውስጥ አጉረው በማሰቃየታቸው ነው፡፡

የዘር ጥላቻ የሰውን ሕሊና ከሚሰውሩ፣ የሰው ልጅ የመጨረሻ አውሬነት አፍጥጦ እንዲወጣ ከሚያደርጉ ክፉ ድርጊቶች አንዱ ነው፡፡ የዘር ጥላቻ ተደጋግሞ እንደታየው በዘር ማጥፋት ይደመደማል፡፡ ቦስኒያ ውስጥ ሰርብ ያልሆኑት ዜጐችን መጨፍጨፍ፣ ኦቶማኖች በአርመኖች ላይ ያደርሱት እልቂት፣ የጀርመን ናዚዎች በይሁዲዎች ላይ የፈጸሙት ግድያና ስቃይ፣ ሳዳም ሁሴን በኩርዶች ላይ ያካሄደው የዘር ምንጠራ፣ ፖል ፖት ያካሄደው ገደብ የለሽ ጭፍጭፋ፣ ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ የፈፀሙት እልቂት፤ በዘር ጥላቻ ላይ ተመስርተው ከተፈፀሙ ግድያዎችና ሰቆቃዎች ውስጥ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ አሳዛኙ ነገር ዘረኛነት ከመሰረተው ስርዓት ተጠቃሚ ያልሆኑ የዚያ ዘር አባላትንም ለብቀላውና ለጥቃቱ ሰለባ ማድረጉ ነው፡፡

የዘር ጥላቻ ከወለዳቸው ዕልቂቶች መሀከል፣ እንስሳት እንኳን ሊፈጽሙት ከማይችሉት የጭካኔ ተግባራት የሚቆጠረው የሩዋንዳው የቱትሲዎች እልቂት ቀዳሚነቱን ሳይዝ አይቀርም፡፡ ሩዋንዳ የቤልጅየም ቅኝ ግዛት በነበረችበት ጊዜ፤ ቅኝ ገዢዎቹ አፍንጫ ሰልካካና ቁመተ ረጃጅምና ከኢትዮጵያ ፈልሰው እንደሄዱ የሚነገርላቸውን ከሕዝቡ 15% የሚሆኑትን ቱትሲዎች ወኪል በማድረግ፣ 85% በሆኑት መደበኛ አፍሪካዊ መልክ ባላቸው ሁቱዎች ላይ አነገሷቸው፡፡ የቱትሲዎችና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከተነሳ፤ ከሃያ ሺህ በላይ ቱትሲዎች እግርና እጃቸውን ታስረው ወደአገራችሁ ኢትዮጵያ ግቡ ተብለው ወደሰሜን ከሚፈስ ቪክቶሪያ ኃይቅ ጋር ከሚቀላቀል ወንዝ ውስጥ መጨመራቸው ይታወቃል፡፡ ሥልጣን በመጠቀም የመንግሥቱን ቢሮክራሲ፣ ንግዱን፣ ትምህርቱን፣ የከብት እርባታውን በመጠቅለል ሁቱዎችን መብት አልባ ዜጐች አደረጓቸው፡፡

ቂም ቋጥረው የኖሩት ሁቱዎች፣ እ.ኤ.አ. በ1962 ዓ.ም. ሩዋንዳ ነፃ ስትወጣ የመንግሥቱን ሥልጣንና መዋቅራት፣ ቢሮክራሲውን፣ የትምህርቱና የንግድ ዘርፎችን በሙሉ ከመጠቅለል አልፈው፤ በቱትሲዎች ላይ የበቀል እርምጃ መውሰድ ጀመሩ፡፡ ቤት ንብረታቸውን ንግዳቸውን የተዘረፉት፣ ከቢሮክራሲው የተባረሩት ቱትሲዎች ደግሞ ወደኡጋንዳ ተሰደዱ፡፡ ወደኡጋንዳ የተሰደዱት ቱትሲዎች ተደራጅተው ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ በጦር ኃይል አማካኝነት ወደ አገራቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ፤ ለዘመናት እያመረቀዘ የመጣው የዘር ጥላቻ፣ አገሪቷ ነፃ ከወጣች ከ32 ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1994 ዓ.ም. ፈንድቶ፣ መቶ በማይሞሉ ቀናት ውስጥ በሩዋንዳዎች ስሌት አንድ ሚልዮን ሶስት መቶ ሺህ ቱትሲዎችና ጥቂት ለዘብተኛ ሁቱዎች፤ ህፃን፣ አሮጊትም ሆነ ሽማግሌ ሳይባል በቆንጨራ ራሳቸውን ለሁለት በመበርቀስ ተጨፈጨፉ፡፡ 

በኢትዮጵያ ፋሽስቱ ደርግ እንዳደረገውም፣ አንዳንዶቹ የሚገደሉበትን ጥይት መግዛት መቻላቸውን እንደ አንድ ልዩና ጥሩ ዕድል ቆጥረውታል፡፡ የሩዋንዳ ሁቱ ጨፍጫፊዎች ተራ የመንደር ወይንም የገዢው ፓርቲ ዱርዬዎች (ኢንተራሃሞዌ) ብቻ ሳይሆኑ፤ የዘር ጥላቻ ምሁር ወይንም መሃይም ስለማይል የታወቁ ምሁራን እና ቄሶች ሳይቀሩ ተሳትፈዋል፡፡ በመሃል ኪጋሊ አንድ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ሁቱ ቄሶች ቱትሲ ቄሶችና ምዕመናንን የጨፈጨፉት የሬሳ ክምር፣ ዛሬም በቤተ-ክርስቲያኑ ውስጥ ይታያል፡፡ ቱትሲዎች ወደኡጋንዳ ሲሰደዱ የ6 ዓመት ሕፃን በነበረው በዛሬው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ መሪነት፣ በጦርነቱ አሸንፈው አገሪቱን ሲቆጣጠሩ፤ ቁጥራቸው የበዛ ሁቱዎች በተራቸው ተገድለዋል፡፡ የእነዚህ የሁለቱ ጐሳዎች መጨፋጨፍ የአገር ጥፋትንና የጅምላ እልቂትን ከመውለዱ ውጪ፤ በዘር ጥላቻ አሸናፊና ተሸናፊ እንደሌለ አመላካች ነው፡፡

ፈረንጆች፣ አንድ ክፉ ነገር አሸንፎ የሚወጣው በጥቂት ሰዎች ዝምታ ምክንያት ነው የሚል አባባል አላቸው፡፡ በዚህ ድሀ ሕዝብ ጫንቃ ተምረው፣ ኑሮአቸውን ካደላደሉ በኋላ አገር አማን ነው ብለው ዝምታን መርጠው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ ቢያንስ የሕሊና ወቀሳ እንደሚነዘንዛቸው ሊክዱ አይችሉም፡፡ በዚህ አደገኛ ጊዜ ዝምታ ወርቅ ሳይሆን ክህደት ነው፡፡ በሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች ስልጣንና ቁሳዊ ጥቅሞች አይናቸውን ጋርዶት፣ ልሳናቸውን ዘግቶት እንደሆነ አይናቸውን መግለጥ ብቻ ሳይሆን ቢበለጥጡት ይበጃቸዋል፡፡ ምክንያቱም ይህች አገር በዘር ጥላቻና በሙስና ምክንያት ብትፈርስና የጅምላ እልቂት ቢከሰት፤ በመጀመርያ የገመዱ ሸምቀቆ የሚገባው በእነርሱ አንገት መሆኑን መዘንጋት የለባቸውምና፡፡ በአገራችን የዘር ጥላቻ በየእለቱ የምናየው ነገር መሆኑ፤ በዚህ ጥላቻ ምክንያትም አገራችን ወደገደል እያመራች መሆኑን አሌ የሚሉ መሪዎችም ሆኑ ምሁራን፤ አውሎ ነፋስ እየመጣ መሆኑንና ሊያደባያት እንደሚችል እያወቀች ራሷን አሸዋ ውስጥ በቀበረች ሰጐን ይመሰላሉ፡፡ ስለዚህ ዘረኝነት የሚያስከትለው አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት የጅምላ እልቂት እርቆ ሳይሄድ፣ መዋጋት ዛሬ እንጂ ለነገ የሚተው አይደለም፡፡ የዚህ ጸሐፊ አስተያየትና ግንዛቤ ስህተት ቢሆን ምንኛ በተደሰተ! ስህተት ባይሆንስ? አንዴ ካንሸራተተ መመለስ እንደማይችል ወይንም እጅግ በጣም አስቸጋሪ ለመሆኑ፤ በመፍረስ ላይ ያሉት እነሶርያ፣ የመሃከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክና ደቡብ ሱዳን (ግብጽ እንኳን ሳትቀር) ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡

የችግራችን መፍትሔ ሁሉም ሊገባው በሚችልበት፣ በሁለት ቃላት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ይህን ያህል የዘር ጥላቻ ተካርሮ ወደ ግጭት ባላመራባት ኢትዮጵያ ቀርቶ፤ በዚያ በጥቂት ቀናት ውስጥ በዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት እልቂት በተፈጸመባት ሩዋንዳ እንኳን፤ ዛሬ በሕዝቡ መሀከል እርቅ ወርዶ፣ ሩዋንዳ በአፍሪቃ የሰላምና የእኩልነት ተምሳሌት ለመሆን ችላለች፡፡ ዛሬ ሩዋንዳዊ እንጂ እገሌ ሁቱ ነው፣ እገሌ ቱትሲ ነው ማለት አጸያፊ ሆኗል፡፡ ስለዚህ፣ ምንም እንኳን መጪዎቹ ጊዜያት አስፈሪ ቢሆኑም ቅሉ፤ ብሔራዊ ዕርቅ በሚሉ ሁለት ቃላት፣ መፍትሔውን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

በአገራችን የኢሕአዴግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕዝባዊ ድርጅቶች ፈቃደኝነት እስካለ ድረስ፣ በቀላሉ እርቅ ወርዶ፣ ለዘር ጥላቻ መንስኤ የሆኑ ነገሮች ታርመው፤ አገራችን ሰላም፣ ፍቅርና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ከመሆን ምንም የሚያግዳት ነገር አይኖርም፡፡ ብሔራዊ ዕርቅ ይውረድ ሲባል፣ “ማን ከማን ጋር ተጣልቷል?” ብሎ መቀለድ፤ በኋላ መሪር ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡ ብሔራዊ መግባባት እንዴት ይመጣል የሚለው፣ በአገሪቱ እኩልነት፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ ያለመ በአገር ደረጃ የሚወሰን ሲሆን፤ ለመነሻነት ያህል ቀጥሎ በተዘረዘሩት መጀመር ይችላል፡፡

ሀ) ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲና የሃይማኖት መሪዎችና አባላት፤ በጠቅላላው ከፖለቲካና ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎችን በሙሉ መፍታት፤

ለ) የጸረ-ሽብርተኛ አዋጅ መሰረዝ፤ እና

ሐ) በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕዝባዊ ድርጅቶች አባላትና መሪዎችን በሽብርተኛነት የተፈረጁትንም አጠቃሎ የያዘ አንድ ጉባዔ በአዲስ አበባ ማካሄድ፤ የሚሉት መነሻ ሊሆኑን ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

ይህ በሀገራችን ያለው ሁኔታም፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊረዳው የሚገባ በመሆኑ፣ ጽሑፉን ያነበበ ለሌላ ቢያስተላልፈው ግንዛቤ ለማስጨበት የሚረዳ ይመስለኛል፡፡
Share:

ተልዕኳችን | Our Mission

“65 ፐርሰንት” ትርጉም? የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ተልዕኳችን ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው። ግባችን ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

What is “65 percent”? 65% of Ethiopia’s population is under 24 years old. Our mission is to model a culture of political concensus for the 65%. Our goal is to advocate for, and initiate reconciliation and consensus among Ethiopians.

Post Archive