Nov 21, 2014

ብሄራዊ መግባባት - ኢሕአዴግ

ብሄራዊ መግባባት ሲባል አንድ አስተሳሰብ በተወሰነ ታሪካዊ ወቅት በሚገኝ ህብረተሰብ ውስጥ ከሞላ ጎደል አብዛኛው ሰው አምኖበት የሚመራበት አስተሳሰብ መሆኑን ለማመልከት ነው:: ይህም በህብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ ተቋማት ይህንኑ አስተሳሰብ ተቀብለው በሱ የሚመሩ መሆናቸውን ከማረጋገጥ ጀምሮ፤ ህጎቹና አሰራሮቹ፤ በሰዎች መካከል ያለው የየእለት ግንኙነት፤ ወዘተ… ይህን አስተሳሰብ ተቀብሎና በሱ እየተመራ የሚከናወንበት ደረጃ ላይ መገኘቱን ያመለከታል፡፡

ትርጓሜውን ይበልጥ ተጨባጭ ለማድረግ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በሀገሪቱ ህገ መንግስትና በመሰረታዊ ፖሊሲዎች ላይ በዋነኝነት ስምምነት ላይ የደረሰበት፤ በዚህ ክልል የሚታዩትን መለስተኛም ሆነ መሰረታዊ ልዩነቶች ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የጋራ ግንዛቤ የተያዘበትን ሁኔታ ለማመልከት ነው ብሄራዊ መግባባት የሚባለው፡፡

የብሔራዊ መግባባትን ምንነት በደንብ ለመረዳት በህብረተሰቡ ላይ በግዴታ የተጫነን አስተሳሰብ ባህሪዎች በንፅፅር ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ በግዴታ የተጫነ አስተሳሰብ ህብረተሰቡ በግድ እንደ መመሪያ እንዲጠቀምበት የተጫነበት ሲሆን ብሄራዊ መግባባት የተፈጠረበት አስተሳሰብ ግን ህብረተሰቡ ቢጠቀምበትም ባይጠቀምበትም ይጠቅመኛል ብሎ አምኖ የሚመራበት እምነት ነው፡፡ በግዴታ የተጫነ አስተሳሰብ ዘላቂነት የሌለው ሲሆን ብሄራዊ መግባባት የተደረሰበት አስተሳሰብ ግን ዘላቂነት ያለው ነው፡፡

ኢሕአዴግ የሚከተለው የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ርዕዮተ አለም ብሔራዊ መግባባትን የግድ ተፈላጊ የሚያደርግና ለብሔራዊ መግባባት መፈጠርም ምቹ ሁኔታን የያዘ ነው፡፡ ይህም የልማታዊ መንግስት ባህሪ ከሆኑት ሶስት ባህሪያት አንዱ የልማታዊነት አስተሳሰብ የበላይነት የተረጋገጠበት ስርዓት ከመሆኑ ጋር ይያያዛል፡፡

እኛ የምንከተለውን መስመር ልዩ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል ከድህነት ወደ ብልፅግና በሚደረገው ሽግግር ህብረተሰቡ ስር ነቀል በሆነ ለውጥ የሚያልፍበት መንገድ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ሕብረተሰቡ ይህን ረጅም ጉዞና ስር ነቀል ለውጥ አምኖ ካልተቀበለውና የራሱ አስተሳሰብና ባህል እንዲሆን ካላደረገው ለውጡን ሊፈፅመው አይችልም፡፡ ይህን መፈፀም የሚቻለው ህብረተሰቡ ለለውጡ ፈቃደኛና ዝግጁ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ እናም ልማታዊ መንግስት ሊኖር የሚችለው በልማታዊነት አስተሳሰብ ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት ሲፈጠር፤ የልማታዊነት አስተሳሰብ የበላይነቱን የተጎናፀፈ /hegemonic/ ሲሆን ነው፡፡

የልማታዊነት አስተሳሰብ የበላይነትም ሆነ ብሄራዊ መግባባት በዋነኝነት የህብረተሰቡን አስተሳስብ በመቅረፅ ላይ ያተኮረ ነው ሲባል ምንም አይነት ነባራዊ መሰረት ሳይኖርው ሊካሄድ ወይም ሊሳካ የሚችል ነው ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ተጨባጭ ልማታዊ ተግባርን ወይም የሕዝብን ብሔራዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ውጤትን ማቅረብን ይጠይቃል፡፡

አንድ አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ የህዝብን የእለት ተእለትና በተወሰነም ደረጃ የመለስተኛና የረጅም ግዜ ተጨባጭ ጥያቄዎችን መመለስ መቻል አለበት፡፡ ህብረተሰቡ አስተሳሰቡን አምኖ ሊቀበለው የሚችለው አኗኗሩን የሚለውጥበት ወይም ከነበረበት ወደ ኋላ የማይመልሰው ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ህብረተሰቡን የሚመራው መንግስት አነሰም በዛም ምልዐተ ህዝቡን የጥቅሙ ተጋሪ ማድረግ በቻለበት ሁኔታ ህብረተሰቡ መንግስት የሚመራበትን አስተሳሰብ ሊቀበል ይችላል፡፡ ሀገሪቱ በማያቋርጥ የለውጥና የእድገት ጉዞ የምትራምድ ስትሆን ህዝቡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከእድገቱ ስለሚጠቀም ከፍተኛ ተስፋ ያሳድራል፡፡

መንግስትን የሚመራው ገዥ ፓርቲ የነደፋቸው ፖሊሲወች በተጨባጭ ብዙሃኑን የሚጠቅም ቅኝት እንዲይዙ ከተደረገም ህብረተሰቡ ከአጭርና ከመካከለኛ ግዜ አኳያ መሰረታዊ ግድፈት ያለበት ስርዓት ቢሆንም እንኳን ከአጭርና ከመካከለኛ ግዜ ጥቅሙ በመነሳት ስርአቱን ሊደግፍና ሊንከባከበው ይመርጣል፡፡ ይህን የመሰለ ሁኔታ ሲፈጠር ህዝቡ ፖሊሲዎቹን በመስማት ብቻ ሳይወሰን በተግባር ውጤታቸውን በማየት ያምንባቸዋል፡፡ በሀገራችን እየሆነ ያለውም ይሄው ነው፡፡

ኢሕአዴግ ይህንን ተገንዝቦ ሰፊ የህዝብ ግንኙነትና የተግባር የተቀናጀ ዘመቻ በማካሄድ ደረጃ በደረጃ የልማታዊነት አስተሳሰብ የበላይነትን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ያለና በተግባርም ውጤት እያስመዘገበ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅታችን የብዙሃኑን ሕዝቦች መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የተሰለፈ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ስለሆነ በኢኮኖሚ እድገቱ የሰፈውን ሕዝብ ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማሳደግ ተረባርቧል፡፡

ኢሕአዴግ ሕዝቡ በተደራጀ አኳኋን በገዛ ፈቃዱ በልማት እንቅስቃሴው በሰፊው እንዲሳተፍ ማድረግ የሚችልና በማድረግም ላይ ያለ ድርጅት ስለሆነም ሕዝቡን ከራሱ ልምድ በመነሳት ወደ ትክክለኛው ድምዳሜ በማድረስና ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ረገድ ከሌሎችም መንግስትን ከሚመሩ ፓርቲዎች የተሻለ ውጤትና ልምድ ማካበት ችሏል፡፡
Share:

ተልዕኳችን | Our Mission

“65 ፐርሰንት” ትርጉም? የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ተልዕኳችን ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው። ግባችን ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

What is “65 percent”? 65% of Ethiopia’s population is under 24 years old. Our mission is to model a culture of political concensus for the 65%. Our goal is to advocate for, and initiate reconciliation and consensus among Ethiopians.

Post Archive