Jul 22, 2026

ከምክክሩ በኃላስ? በያዬ አበበ

ሀገራዊ ምክክሮች የማይሳኩት ከምክክር በፊት ፣ በምክክር ወቅት እና ከምክክር በኃላ በሚከሰቱ እንቅፋቶች ነው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ቅድመ ዝግጅት ሂደት አንፃራዊ ቅቡልነት አትርፏል። የተጀመረው ምክክርም እንደዛው እንደሚሆን ይጠበቃል።

የምክክሩ ውጤት አፈፃፀም ግን ሌላ ጉዳይ ነው።

የሀገራዊ ምክክሩ ውጤት ብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ ጀምሮ ላለፉት ስድስት አመታት ካጋጠሙት ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ ትልቁ ውስጣዊ ፈተናው ይሆናል።

በፓርቲው ውስጥ በሚገኙት በሕብረ-ብሔራዊ (multi nationalists) እና በንዑስ-ብሔርተኛ (ethno nationalists) መካከል ለሚቀጥሉት ወሳኝ አሥርት ዓመታት ስለኢትዮጵያ ባላቸው የማይታረቅ የርዕይ ልዩነት የተነሳ ገዢው ፓርቲ የመከፋፈል አዝማሚያው ከፍተኛ ነው።

​የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ሰሞኑን ‘የኦሮሚያ ክልል እንዳይኖር የሚፈልጉ አሉ’ ማለታቸው ሚጠቁመው የፓርቲው ልዩ ልዩ አንጃዎች ከሀገራዊ ምክክሩ የሚጠብቁት ውጤት እንዳለና ፡ በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ የምክክሩ ውጤት ሚፈጥረውን ውስጣዊ ክፍፍል ነው።


​የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ግጭቶች ባለፉት 8 ዓመታት መቋጫ አላገኙም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውክልና (mandate) ባልሰጣቸው የራሳቸው የትርፍ ጊዜ ፕሮጀክቶች (pet projects) ላይ ባተኮሩበት ወቅት ከድህነት ወለል በታች የሆኑ ዜጎች ቁጥር እጂግ ጨምሯል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን የማያከብር—የግል ፕሮጀክቶቹን የገንዘብ ምንጭ ለመግለጽ ፈቃደኛ ያልሆነ—አቅም የሌለው እና ርዕዮተ-ዓለማዊ ብስለት የጎደለው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለበት ሁኔታ፣ ለ8 ዓመታት የሰነበቱት የአገር ውስጥ አለመረጋጋቶች ላይ የተከፋፈለ ገዢ ፓርቲ ጋር ሲጨመርበት የሀገሪቱ ቀውስ ይበልጥ እየተባባሰ ይሄዳል።

​እንዲህ ዓይነቱ ሀገርዊ ቀውስ ባለሃብቶች ውስጥ ስጋትን ይጨምራል፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የኑሮ ውድነት መከራ ያባብሳል፣ ይህም ውሎ አድሮ ወደ ሁከትና ተቃውሞ ያመራል።

​ባለፉት 8 ዓመታት በአብዛኛው የከሸፈው፣ መርህ አልባ እና ርዕዮት የለሹ የአብይ አመራር ላይ አሁን ያለው ተለዋዋጭ የምስራቅ አፍሪካ፡ የመካከለኛው ምስራቅ እና የዓለም አቀፍ ጂኦፖለቲላዊ አለመረጋጋት ሲጨመሩበት ለኢትዮጵያ ሕልውና ትልቅ ፈተና ሆኗል።

​እርግጥ ነው ለሀገራዊ መግባባት ስንሟገት ለቆየነው ወገኖች ምክክሩ መልካም ምዕራፍ ነው። ሀገራዊ ምክክሩ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ያለበትን የቅቡልነት ማነስ ለመገንባት የሚያስችል አቅም ያለው ከመሆኑ ባሻገር ለአገሪቱ ሰፊ የወጣት ማኅበረሰብ የውይይት እና የመግባባት ባህልን ለማዳበር አዎንታዊ እርምጃ ነው።

​ነገር ግን የሀገራዊ ምክክሩ ውጤት በገዢው ፓርቲ ላይ ስለሚኖረው አንድምታ በጥንቃቄ አርቆ ሳያስቡ፣ እንዲሁም አቅም እና ርዕዮታዊ ብስለት የሌለውን የገዢውን ፓርቲ መሪ ሳይቀይሩ ኢትዮጵያ የሀገራዊ ምክክሩን ፍሬ አታጭድም፣ ይልቁንም ወደ ተባባሰ ሁከት ትገባለች።

የሌሎች ሀገራት የምክክር ተሞክሮ እንደሚያሳየው ቅድመ-ምክክር ዝግጅት እና የምክክር ክንዋኔዎች ብቻ ሳይሆኑ ድህረ ምክክር አፈፃፀምም ለምክክር ውጤታማነት ወሳኝ ነው። ዛሬ ባለው የአቢይ ደካማ አመራር በፈጠረው ሀገራዊ ቀውስ አውድ ውስጥ የምክክሩ ውጤትን ለመተግበር ማሰብ ከንቱ ድካም ነው።

Share:

ተልዕኳችን | Our Mission

“65 ፐርሰንት” ትርጉም? የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ተልዕኳችን ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው። ግባችን ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

What is “65 percent”? 65% of Ethiopia’s population is under 24 years old. Our mission is to model a culture of political concensus for the 65%. Our goal is to advocate for, and initiate reconciliation and consensus among Ethiopians.

Post Archive